በአቶ ዓባይ ጸሃዬ የቀረበውና አስፈጻሚ አካላት ከህግ በላይ ሆነዋል የሚለውን ጥናት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይማሪያም ደሳለኝ አጣጣሉት

ኢሳት (ሚያዚያ 12 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ የፖሊሲ ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር በአቶ ዓባይ ጸሃዬ የቀረበውና አስፈጻሚው አካላት ከህግ በላይ ሆነዋል የሚለውን ጥናት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይማሪያም ደሳለኝ አጣጣሉት።

አቶ ሃይለማሪያም ከተመረጡ የሃገር ውስጥ ጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ በቅርቡ በአቶ አባይ ጸሃዬ እና በተወሰኑ የመንግስት ተጠሪዎች የቀረበውን ጥናት አላውቀውም፥ ትክክለኛ ግምገማም አይደለም ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።

ይህን የሚያመለክተው የአቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ መግለጫ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በሚተላለፈው ቴሌቪዥን ተቆርጦ እንዲወጣ ተደርጓል።

ኢ. ኢን. ኤን. የተባለውና በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካዔል የሚመራ አዲሱ የኢህአዴግ ቴሌቪዥን ግን በዚያ ዘገባው ጉዳዩን ይፋ አድርጎታል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ሃይለማሪያምና የአቶ አባይ ፀሃዬ የሃሳብ ልዩነት በህወሃት ውስጥ ሁለት ጎራ መኖሩን አመላካች መሆኑን ታዛቢዎች ይናገራሉ።