በአሶሳ ዩኒቨርስቲ የተጠራው አጠቃላይ ስብሰባ በተቃውሞ ተቋረጠ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 25/2010)በአሶሳ ዩኒቨርስቲ የተጠራው አጠቃላይ ስብሰባ በተቃውሞ መቋረጡ ተሰማ።

በዩኒቨርስቲው የመማር ማስተማር ሂደት ላይ ከተማሪዎች ጋር ለመወያየት የተጠራው ስብሰባ ወደተቃውሞ መድረክ በመለወጡ መቀጠል ሳይችል ቀርቷል።

የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት ተማሪዎቹ ያነሷቸው ጥያቄዎች የፖለቲካና የአካዳሚክ ነጻነቶችን የተመለከቱ በመሆናቸውና ከሰብሳቢዎቹ አቅም በላይ በመሆኑ ስብሰባው ሊቋረጥ ችሏል።

የአንድ ለአምስት አደረጃጀትን የተቃወሙት ተማሪዎቹ የትምህርት ጥራትንም አንስተው የኢትዮጵያ የወደፊት ሁኔታ እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።

የስብሰባው ዓላማ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተማሪዎች ከተዘጋጁትና በህወሀት መንግስት ከተቀረጹት የውይይት መድረኮች የተለየ አይደለም።

በመላ ሀገሪቱ የተቀሰቀሰውን የህዝብ ተቃውሞ ለማስተንፈስና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን ከተቃውሞ እንቅስቃሴ ውጭ ለማድረግ በሚል በተከታታይ የሚዘጋጁት መድረኮች አካል የሆነው የአሶሳው ውይይት ትላንት ድረስ በከፍተኛ ተቃውሞ ሲካሄድ ቆይቶ ሊቋረጥ መቻሉን ነው የኢሳት ምንጮች የገለጹት።

ተማሪዎቹ እንዲህ ዓይነት መሰል ውይይት በየዓመቱ የሚዘጋጅ በመሆኑ የተለየ ነገር ከሌለ ለምን አስፈለገ የሚል ጥያቄ በመጀመሪያዎቹ የውይይቱ ቀናት ያነሱ ሲሆን ከመድረክ የተሰጣቸውም ምላሽ ተመሳሳይ ሆኗል።

ውይይቱ በዩኒቨርሲቲው አጠቃላይ እንቅስቃሴ ላይ በማተኮር እንዲካሄድ ከመድረክ አቅጣጫ የተሰጠ ቢሆንም ተማሪዎቹ መሰረታዊ የሆኑ ጥያቄዎችን በማንሳት ሰብሳቢዎቹን ወጥረው መያዛቸው ተገልጿል።

በተለይም በዩኒቨርስቲው ተግባራዊ የተደረገውን አንድ ለአምስት አደረጃጀት ተማሪዎቹ በጽኑ የተቃወሙት ሲሆን ይህ አደረጃጀት ለግብርና ስራ እንጂ ለትምህርት ተቋማት አይሰራም ሲሉ አጣጥለውታል።

ተማሪዎቹ አጠቃላይ የኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት ላይ ያነሱት ጥያቄ በተሰብሳቢዎች ከፍተኛ ድጋፍ አስገኝቷል።

ለመምህርነት ሙያ የተሰጠው ቦታ አነስተኛ ነው ትውልድ ለሚቀርጽ ሙያ የሚሰጠው ትኩረት ከሌሎቹ አንጻር እጅግ ዝቅ ያለ እንደሆነ የጠቀሱት ተማሪዎቹ የነገ የኢትዮጵያ እጣ ፋንታ ያሳስበናል ሲሉም ገልጸዋል።

በስብሰባው ላይ ሌላው የተነሳው የተማሪዎቹ ብሶት ተምረው ስራ የማግኘታቸው እድል የተመናመነ መሆኑ ነው።

እኛ ባልተሟላና ጥራቱን ባልጠበቀ ሁኔታ ተሰቃይተን ተምረን ገንዘብ ያላቸው ቤታቸው ቁጭ ብለው በፎርጅድ የትምህርት ማስረጃ ስራ ይቀጠራሉ ሲሉ በምሬት ገልጸዋል።

ስብሰባው በዚህ ሁኔታ መቀጠል ባለመቻሉ ትላንትና መቋረጡ የተገለጸ ሲሆን ዛሬ ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል።