በአርበኞች ግንቦት7 አባልነት በተከሰሱት ላይ ምስክሮች ተሰሙ

ሐምሌ ፲ ( አሥር ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የከፍተኛው ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት አቃቢ ህግ በአርበኞች ግንቦት7 ስም በከሰሳቸው በእነ ትንሳኤ በሪሶ ላይ የደረጃ ምስክሮችን አቅርቦ አሰምቷል።
የቀረቡት ሁለቱም ምስክሮች ማዕከላዊ ዐንጀል ምርመራ ቃላቸውን ሲሰጡ ታዝበናል ያሉ የደረጃ ምስክሮች ናቸው። እንዳልክ ዘርፉ የተባለው በአፍሪካ ህብረት ሰራተኛው በአቶ ትንሳኤ በራሶ ላይ የመሰከረ ሲሆን፣ አቶ ትንሳኤ “አይ ኤስ በኢትዮጵያውያን ላይ የፈፀመው በደል መንግስት ትኩረት ባለመስጠቱ የግንቦት 7 አባል ሆኛለሁ ብሎ ሲናገር” ታዝቤያለሁ ብሏል።
ስጋቱ ከድር እንደሚባል የገለፀው ሁለተኛው ምስክር በ6ኛ ተከሳሽ ኤርሚያስ ፀጋዬ ላይ የመሰከረ ሲሆን፣ ማንነቱን ለመለየት መታወቂያ እንዲያሳይ ሲጠየቅ የስራም ሆነ የቀበሌ መታወቂያ እንደሌለው ገልፆአል። ምስክሮቹ በተደጋጋሚ የአቃቤ ህግ ምስክር ሆነው በመቅረብ የሚመሰክሩ ናቸው።
አቶ ትንሳኤ በሪሶ ከአሁን ቀደም አብርሃም ይታገሱ እና ማስረሻ ዮሃንስ የተባሉ አብረውት ታስረው የነበሩ ግለሰቦች በዝግ ችሎት ለድርጅቱ ካራቴ እንድናሰለጥንለት መልምሎናል ብለው መስክረውበታል።ሁለቱም ምስክሮች ማዕከላዊ ውስጥ እስረኛች በግድ እንዲመሰክሩ የሚገደዱበት ጣውላ ቤት የተባለ የእስር ክፍል ውስጥ ታስረው እንደነበር ታውቋል።
ትንሳኤ በሪሶ፣ ዳንኤል ተስፋየ፣ ግሩም አስቀናው፣ቴዎድሮስ አስፋው፣ ፍሬው ተክሌ፣ ኤርሚያስ ፀጋየ፣ አሰጋ አሰፋ፣ ፡ጌታቸው ይርጋ፣ ሽቴ ሙሉ፣ እና ሀይሌ ማሞ በተመሳሳይ መዝገብ ተከሰው የነበረ ሲሆን፣ አቶ ሀይሌ የቂሊንጦ ቃጠሎ ወቅት የተገደሉት ሻለቃ ይላቅ አቸነፈ ጉዳይ የህዝብ ቁጣ እንዳይቀሰቅስ በሚል የተፈቱ ናቸው። አቶ ሀይሌ በተጨማሪም በኢንስፔክተር አበበ የሁዋላ ስር ተከሰው የነበሩ5 ግለሰቦች እንዲሁም ከተገደሉት ጋር በአንድ መዝገብ ተከሰው የነበሩት አቶ አዋጁ አቡሃይን ጨምሮ ህዝብን ለማረጋጋት በሚል ከጎንደር ተይዘው በሽብር ወንጀል ተከሰው የነበሩት ግለሰቦችም ተፈትተዋል። ከሻለቃ ይላቅ በተጨማሪ ሰጠኝ ሙሉ የተባለ የአርማጭሆ ተወላጅም ተገድሏል። ሻለቃ ይላቅ በአካባቢው ህዝብ ትልቅ ተቀባይነት እንደነበራቸው ይነገራል።