በአማራ ክልል የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታ መስፋፋቱ ተገለጸ

(ኢሳት ዜና– ሐምሌ 19/2009)በአማራ ክልል በአምስት ዞኖችና 35 ወረዳዎች የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በሽታ ተስፋፍቷል ሲሉ ነው የኢሳት ምንጮች በመረጃቸው ያመለከቱት።

በአሁኑ ወቅትም በአንዳሳ፣ወንቅሸት፣አቡነሃራና ወረብ ከሚባሉ አካባቢዎች በበሽታው ተጠቅተው የመጡ 17 ሰዎች በሆስፒታሉ ተኝተው እየታከሙ መሆናቸው ተገልጿል።

በባህር ዳር ከተማ ወደ አዲስ አለም ሆስፒታል ከመጡ ታካሚዎችም 15 ሰዎች በወረርሽኙ መያዛቸው መረጋገጡን ለማወቅ ተችሏል።

በአማራ ክልል ጤና ቢሮ አንድ የስራ ሃላፊ ለመገናኛ ብዙሃን እንደገለጹት የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት ከተቀሰቀሰባቸው አካባቢዎች 1 ሺ 229 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው ተረጋግጧል።

ወረርሽኙ በክልሉ 5 ዞኖችና 35 ወረዳዎች መከሰቱን የጤና ቢሮው ቢገልጽም የዞኖቹንና ወረዳዎቹን ስም ግን ከመጥቀስ ተቆጥቧል።

በበሽታው ተይዘዋል ከተባሉ ሰዎች 1 ሺ 205ቱ ታክመዋል ቢባልም በወረርሽኙ ስለሞቱ ሰዎችም ሃላፊው ለመናገር እንዳልፈለጉ ከዘገባው ለመረዳት ተችሏል።

በአማራ ክልል የኮሌራ በሽታ በብዙ አካባቢዎች መከሰቱንና በርካታ ሰዎችም ከዚሁ ጋ ተያይዞ ህይወታቸውን ማጣታቸውን የኢሳት ምንጮች ይናገራሉ።

ይህም ሆኖ ግን በሽታውን የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት /አተት/በሚል ለመሸፋፈንና የሞቱ ሰዎችም በዚሁ ወረርሽኝ ስለመሞታቸው ለመግለጽ አለመፈለጉ አገዛዙ ለሕዝቡ ህይወት ደንታ እንደሌለው ያሳያል ሲሉ ምንጮቻችን ጨምረው ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ህብረተሰቡን ከወረርሽኙ ለመጠበቅ የግል ንጽህናውን ይጠብቅ ከማለት ባለፈ የተጠናከረ የመከላከል እርምጃ እየወሰደ አለመሆኑን ከአካባቢው ያገኘንው መረጃ ያመለክታል።