በአማራ ክልል የተሰጡት የ10ኛና የ12 ኛ ክፍል ፈተናዎች በርካታ ችግሮች ነበሩባቸው ተባለ

ሰኔ ፮ (ስድስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በዚህ አመት የተሰጡት የ10ኛና የ12ኛ ክፍል ፈተናዎች የዓመተ ምሕረት መቀላቀል፣ የፈተና መለያ ኮድ መዘበራረቅና የጥያቄ መጉደል ታይቶባቸዋል።
ወኪላችን ስማቸውና ድምጻቸው እንዳይተላለፍ የጠየቁ ተማሪዎችና ምሁራን በመጥቀስ እንደዘገበችው ወደ አማራ ክልል በተላኩ የ10ኛ ክፍል የመፈተኛ ወረቀቶች ላይ ጉልህ የሆኑ ስህተቶች ተከስተዋል። በመጀመሪያው ቀን የተከሰተው ስህተት ተማሪዎች በድንጋጤ ቀሪዎችን ፈተናዎች ተረጋግተው እንዳይፈተኑ እንዳደረጋቸው ቅሬታ አቅራቢዎች ይገልጻሉ።
በአማርኛ ቋንቋ ፈተና ላይ የተፈጠረውን ስህተት ሲያስረዱም “የፈተና ጥራዝ መለያ- 013” በውስጥ ገጹ እና ከጥራዙ ሽፋን ላይ ደግሞ “Booklet Code: 011” የሚለው ፈተና ላይ በተራ ቁጥር 17 እና 23 ላይ የቀረቡ ጥያቄዎች ተመሳሳይ ናቸው፡፡

በዚሁ ፈተና በተራ ቁጥር 17፣ 18፣ 19 እና 20 በድጋሜ የተለያዩ ጥያቄዎችን ይዘው በገጽ 5 እና 6 ላይም ይገኛሉ፡፡ የገጽ 5 ተራ ቁጥር 20 እና ገጽ 7 ያለው ተራ ቁጥር 21 የያዟቸው ጥያቄዎችና የመልስ አማራጮችም አንድ ዓይነት ናቸው፡፡ የገጽ 5 ተራ ቁጥር 19 እና የገጽ 7 ተራ ቁጥር 22ትም እንዲሁ አንድ ዓይነት ናቸው፡፡
‟የአማርኛ ቋንቋ ፈተና መለያ ኮዱ ከሽፋኑ እና በውስጥ ገጾች 6፣ 7፣ 14፣ 15፣ 22 እና 23 ላይ ኮዱ 011 ሲሆን በሌሎች የውስጥ ገጾች 1፣ 2፣ 3፣ 4፣ 5፣ 8፣ 9፣ 10፣ 11፣ 12፣ 13፣ 16፣ 17፣ 18፣ 19፣ 20፣ 21 እና 24 ላይ ደግሞ መለያ ኮዱ 013 በመሆኑ ይህ ፈተና የሚታረመው በየትኛው የፈተና ኮድ ነው፡፡ ”በማለት ምሁራኑ ይጠይቃሉ፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ በአስራ ሁለተኛ ክፍል የታሪክና ስነ-ዜጋ ፈተናዎች ስህተቶች እንደተፈጠሩበት የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢ ምሁራን፣ ስህተቱን ከቀላል ግደፈት ጋር አላያያዙትም።
በተለይ አምና በክልሉ በተደረገው ፈተና 67 በመቶ የሚሆኑ የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች መውደቃቸው ፣ ዘንድሮ ደግሞ የ 10ኛ ክፍል የአማርኛ ቋንቋ እና የ12ኛ ክፍል የስነ-ዜጋና ታሪክ ትምህርቶች ስህተት የተሞላባቸውን ጥያቄዎች ይዘው መምጣታቸው ሆን ተብሎ የተደረገ ነው ብለው እንዲያምኑ አድርጓቸዋል።

“የተደጋጋሙ ጥያቄዎችን በማቅረብ እና የፈተና መለያ ቁጥሮችን በመዘበራረቅ ተማሪዎች ለምን ትምህርታቸውን ተረጋግተው እንዳይፈተኑ ለማድረግ ተፈለገ?” ሲሉ የሚጠይቁት መምህራኑ፣ ጉዳዩ ሆን ተብሎ የተደረገ ሊሆን ስለሚችል አስፈላጊው ምርመራ ሊደረግ ይገባዋል ብለዋል።
አገራቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ የ10ኛ እና 12ኛ ክፍሎች ፈተናዎች ያለምንም ችግር ተጠናቀዋል ሲል መግለጫ ሰጥቷል።