በአማራ ክልል ዕምነት አልተጣለባቸውም የተባሉ የፖሊስ አመራሮች ከሃላፊነትና ከደረጃቸው ዝቅ ተደረጉ

ኢሳት (ግንቦት 7 ፥ 2009)

በአማራ ክልል ከተካሄደው የጸጥታና ደህንነት ግምገማ ጋር በተያያዘ በህወሃት ዕምነት አልተጣለባቸውም የተባሉ የፖሊስ አመራሮች ከሃላፊነትና ከደረጃቸው ዝቅ ተደረጉ።

ከክልሉ የፖሊስ አመራሮች ከስራ የተሰናበቱም ይገኙበታል። በባህርዳርና በጎንደር ከተፈጸሙት የቦምብ ጥቃቶች ጋር በተያያዘ የአካባቢው ጸጥታ አልተቆጣጠራችሁም የተባሉት የክልሉ ፖሊስ አባላት ስም ዝርዝር ኢሳት ደርሶታል።

የአማራ ክልል አመራር አባላት ከስራ ደራጃቸው ዝቅ የተደረጉትና የተባረሩት የትምክህት አስተሳሰብ ሰለባ ናችሁ በሚል እንደሆነ የኢሳት ምንጮች ይገልጻሉ። ጥፋታቸው ደግሞ የቦምብ ፍንዳታ አልተቆጣጠራችሁም በሚል በትምክተኝነት ስለፈረጇቸው መሆኑት ተገልጿል።

በባህርዳርም ሆነ በጎንደር በተከታታይ ከተፈጸሙ የቦምብ ጥቃቶች ጋር በተያያዘ ከድርጊቱ ጀርባ እጃቸው አለበት የተባሉ እንዳሉም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። 72 የባህርዳር ነጋዲዎች አመፅ እንዲቀሰቀስ ይደግፋሉ ተብለው እንዲታሰሩ ሲወሰን አግባብ አይደለም በማለታቸው አገዛዙ የጠመዳቸው እንዳለ ተገልጿል። አንዳንዶቹ የአገዛዙ አገልጋዮች የነበሩ ናቸው።

በህወሃት አመራሮች ግፊት በተደረገው የጸጥታና ደህንነት ግምገማ ከደረጃቸው ዝቅ የተደረጉና የተባረሩ የፖሊስ አመራር አባላት ስም ዝርዝር ለኢሳት ደርሷል። እነዚሁም ኮማንደር ደረጃ አቻምየለህ ከመምሪያ ሃላፊነት ወደ መዝገብ ቤት አደረጃጀት፣ ኮማንደር ቢያዝን ማንአሳብ ከፖሊስ መረጃ ወደ 24 ሰዓት የመረጃ ክፍል፣ ኮማንደር አንማው አለሜ ከወንጀል መከላከል ወደ ሰው ሃይል ማደራጃ፣ ኮማንደር ካሴ ከጽህፈት ቤት ሃላፊነት ወደ ሬዲዮ መገናኛ፣ ኮማንደር ስማቸው ከወንጀል መከላከል ወደ አሻራ ክፍል ከደረጃ ዝቅ ብለው የተመደቡ ናቸው። በባህርዳር ፖሊስ መምሪያም ኮማንደር ጥበቡ ሃይሌ፣ ኮማንደር ውበቱ አለ እና ኮማንደር ሙሉጌታ አያልነህ በቅርቡ ከሃላፊነት የሚነሱ መሆናቸው ተነግሯል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር እና የህወሃት አባል የሆነው ደስዬ ደጀን የተባለው አመራር ከመባረርና ከስራው በስተጀርባ ዋነኛው ተዋናይ መሆኑ ታውቋል። የአማራ ክልል የጸጥታና የደህንነት አመራሮች እንዲባረሩ ግምገማውን ከበስተጀርባ የሚመሩት የህወሃቶቹ ቁጥጮ አመራሮች አቶ አባይ ጸሃዬና አቶ ስብሃት ነጋ መሆናቸውን ከምንጮቻችን ያገኘነው መረጃዎች የመለክታሉ።