በአማራ ክልል አጠቃላይ አድማ ለመጥራት እንቅስቃሴ መጀመሩ ታወቀ

(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 17/2009) በባህርዳር በግንቦት 20 ክፍለከተማ የተጠራው ስብሰባ በተቃውሞ ተቋረጠ።
ከመነሻው በአንድ ነጋዴ ተቃውሞ ሲቀርብ በተቋረጠው ስብሰባ ላይ ሁለት ነጋዴዎች አስተባብራችኋል ተብለው ታስረዋል።

በዘፈቀደ የተጣለውን ግብር በግዳጅ ለማስከፈል የተጠራውን ይህን ስብሰባ ነጋዴ መቃወም ሲጀምር የልዩ ሃይል አከባቢውን መውረሩን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
በአማራ ክልል አጠቃላይ አድማ ለመጥራት እንቅስቃሴ መጀመሩንም የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
በደምበጫና ቡሬ አካባቢ ዛሬ ሱቆችና መደብሮች ተዘግተው እንደነበረም ታውቋል።
ዛሬ በኦሮሚያ የተጀመረው አድማ በአማራው ክልል የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ የፈጠረ ሲሆን በአንዳንድ አካባቢዎች ተሽከርካሪዎች በፖሊስ አጀብ ካልሆነ ማለፍ እንዳልቻሉም ተገልጿል።

ዛሬ በባህርዳር በግንቦት 20 ክፍለ ከተማ የተጠራውና ከግብር ጋር የተያያዘው ስብሰባ ከመነሻው የተቋረጠው በነጋዴዎች ተቃውሞ ከቀረበ በኋላ ነው።
የግብር ተመን እንዲስተካከል የጠየቁ ነጋዴዎች ስብሰባው ሲጠራ ለውጥ እንደተደረገ ተነግሯቸው ነበር። በዘፈቀደ የተጣለው ግብር ይስተካከላል የሚል ቃል ተገብቶላቸው እንደነበረ የተገለጸ ሲሆን ስብሰባ ሲጀመር ግን ምንም ለውጥ እንዳልተደረገና የተጣለባቸውን ግብር እንዲከፍሉ ከመድረክ በመንግስት ሃላፊዎች ሲነገራቸው ተቃውሞ መቀስቀሱን ነው በስብሰባው የነበሩ አንድ ነጋዴ ለኢሳት የገለጹት።

ስብሰባውን በግድ ትከፍላላችሁ ብሎ መጀመር ንቀት ነው ያሉት እኒህ ነጋዴ። ለውጥ ለሌለው ነገር ለምን ውድ ጊዜያችንን ታባክናላችሁ በሚል የተጀመረው ተቃውሞ በኋላ አንድ ተሳታፊ ንግግር ማድረግ ሲጀምሩ ስብሰባው መበጥበጡንና መቋረጡን ለማወቅ ተችሏል።

በአከባቢው የነበሩ የፌደራል ፖሊሶች በፍጥነት አዳራሹን በመውረር ሁለት ሰዎችን አስረው መውሰዳቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ድምጽ
የባህር ዳር ነጋዴዎች የተጋነነውን ግብር እንደማይከፍሉ ቀደም ሲሉ የያዙትን አቋም ዛሬ በተጠራው ስብሰባ ላይ ማንጸባረቃቸው የተገለጸ ሲሆን መንግስት ካልከፈላችሁ ትታሰራላችሁ በሚል እያስፈራራ ነው ተብሏል።
ባህርዳር ከግብር ተመን ጋር በተያያዘ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ከተማዋን እያሽመደመዳት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ከነሀሴ አንድ ወዲህ ባህርዳር መረጋጋት የተሳናት ሲሆን ከ500 በላይ ነጋዴዎች ታስረው በየቀበሌው እስር ቤት ውስጥ እንደሚገኙ መዘገቡ ይታወሳል።

በአማካይ ከ10ሱቆች ሰባት ያህሉ አሁንም ድረስ ያልተከፈቱባት ባህርዳር በኢኮኖሚው ከሚደርስባት ከፍተኛ ኪሳራ በላይ የህዝቡ ሰላም ማጣት አንገብጋቢው ጉዳይ ሆኗል ይላሉ ነዋሪዎች።
በሌላ በኩል ላለፉት 3 ሳምንታት ያዝ ለቀቅ እያደረገ ሲካሄድ የነበረውና በተለይ በምስራቅ ጎጃም በበርካታ አከባቢዎች የተደረገው የስራ ማቆም አድማ በተወሰኑ ከተሞች በከፊል እንደቀጠለ መረጃዎች ያሳያሉ።

በደምበጫን ዛሬም ድረስ ያልተከፈቱ የንግድ ቦታዎች እንዳሉ ተገልጿል። በቡሬም እንዲሁ ሱቆችና መደብሮች እንደተዘጉ ታውቋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በኦሮሚያ ዛሬ የተጀመረው አድማ በተለያዩ የአማራ አከባቢዎች ተጽእኖ የታየበት ሲሆን ወደ ኦሮሚያ ክልል የሚያመሩና ከኦሮሚያ ወደ አማራ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴአቸው ተገትቶ መዋሉን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ከባህርዳር ወደ ነቀምት የሚደረገው ጉዞ ከትላንት ጀምሮ የተቋረጠ ሲሆን፡ ከባህርዳርና አጎራባች አካባቢዎች ወደ ወለጋ የተለያዩ ከተሞች የሚያመሩ የህዝብ ማመላለሺያ አውቶብሶች ዛሬ ሙሉ በሙሉ ቆመው መወላቸው ታውቋል።
ድምጽ
በሌላ በኩል በአማራ ክልል አጠቃላይ አድማ ለመጥራት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን በህቡዕ የሚንቀሳቀሱ ወጣቶች በበተኑት ወረቀት ላይ አስታውቀዋል። በተናጠል የሚደረገው ትግል በአንድ ላይ እንዲሆን የሚያስችለውን ይህን እንቅስቃሴ በቅርቡ ይፋ እንደሚያደጉትም ገልጸዋል።
ድምጽ