በንፋስ ስልክ ክፍለከተማ ስር የሚገኙ ነዋሪዎች ግራ መጋባታቸውን ገለጹ

የካቲት ፲፮ ( አሥራ ስድስት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአዲስ አበባ በንፋስ ስልክ ክፍለከተማ አንዳንድ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ንብረታቸውን በ7 ቀናት ውስጥ አንስተው መሬቱን እንዲያስረክቡ ከሰበታ ከተማ አስተዳደር ደብዳቤ እንደተሰጣቸው እና በተጠቀሰው ቀናት ውስጥ ንብረታቸውን የማያነሱ ከሆነ አስተዳድሩ እርምጃ እንደሚወስድ እንደተነገራቸው ለኢሳት ገልጸዋል። በከፍተኛ ደረጃ የታጠቁ የኦሮምያ ክልል ፖሊሶች በግለሰቦች ቤት እየሄዱ ቤታቸውን አፍርሰው እንዲወጡ ሲያስጠነቅቁና ደብዳቤም በግድግዳዎች ላይ ሲለጥፉ አርፍደዋል። ፖሊሶቹ የኦሮምያ ክልል አቦ ሰፈር፣ የቻይና ሪል ኢስቴት እና ካቶሊክ ዩኒቨርስቲ የሚገኙባቸው ቦታዎች እንዲሁም ሙዚቃ ሰፈር ጀርባ ያሉ ነዋሪዎች ቦታዎቹ የአዲስ አበባ መስተዳደር ይዞታዎች አለመሆናቸውን በመጥቀስ ፣ በዚህ አካባቢ የሰፈሩ ሰዎች ሁሉ ቦታውን እንዲለቁ ሲያስጠነቅቁ አርፍደዋል።
ጉዳዩ ያስደነገጣቸው ነዋሪዎች ለመስተዳድሩ አቤት ካሉ በሁዋላ፣ ማምሻውን የፌደራል ባለስልጣናትና ወታደራዊ መኮንኖች ወደ ሰበታ አስተዳደር በመሄድ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፣ የከተማው ስራ አስኪያጅ ፖሊሶችን ማን እንደላካቸው እንደማያውቅ እንዲሁም ደብዳቤው ላይ ፊርማ የሌለው መሆኑን በመግልጽ ራሱን ለመከላከል ሞክሯል። ውዥንብሩ ግን አሁንም ቀጥሎአል። አንዳንድ ከቦታቸው እንዲሱ የታዘዙ ነዋሪዎች ከ40 አመታት በላይ ለአዲስ አበባ መስተዳደር ግብር ሲገብሩ መኖራቸውን ይገልጻሉ።
በሌላ በኩል ዛሬም ቤቶችን የማፍረስ ዘመቻው ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ በቦሌ ክፍለከተማ ወረዳ 9 ልዩ ስሙ ቀጠና 9 ፣ ከ300 ቤቶች በላይ መፍረሳቸው ታውቛል።