በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በተቀሰቀሰው የኮሌራ በሽታ በትንሹ 10 ሰዎች ሞቱ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 30/2010) በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በተያዘው ወር በተቀሰቀሰው የኮሌራ በሽታ በትንሹ 10 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ።

በክልሉ መተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ ጉብላክ ከተማ በተቀሰቀሰው በዚሁ የኮሌራ በሽታ በከተማው የሚገኘው ጤና ጣቢያ ሌላ አገልግሎት እንዳይሰጥ መከልከሉም ታውቋል።

በተለይ በአርሶአደሮች መንደር በሽታው የተስፋፋ በመሆኑ የሟቾች ቁጥር ከዚህ በላይ ሊሆን እንደሚችል ይነገራል።

በተመሳሳይ ወረርሽኙ በድሬደዋ ከተማም መቀስቀሱንና በበሽታው 127 ሰዎች መጠቃታቸው ታውቋል።

በመንግስት በኩል በይፋ የተገለጸ ነገር ባይኖርም የአካባቢው ባለስልጣናት አተት እንጂ ኮሌራ አይደለም ማለታቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

ወረርሽኙ ኮሌራ ስለመሆኑ ባለሙያዎችም ይመሰክራሉ። መንግስት ግን አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት ነው የሚለውን የቀደመ አቋሙን አለቀቀም።

የኢሳት የመረጃ ምንጮች እንደገለጹት የወረርሽኙ ምልክት መታየት የጀመረው ካለፈው ዓመት ሀምሌ ወር ጀምሮ ነበር።

ለወረርሽኙ ሌላ ስም እየተሰጠው በወረዳው ባልስልጣናትም እየተደበቀ ቆይቶ ከያዝነው ወር መስከረም አንስቶ የሰው ህይወት መጥፋት ሲጀምር ጉዳዩ ትኩረት አገኘ።

በመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ ጉብላክ ከተማ ከአንድ ወር በላይ በዘለቀው የኮሌራ ወረርሽኝ አልጋ ከያዙት በመቶዎች ከሚቆጠሩት ህሙማን በተጨማሪ ከ10 ያላነሱ ሰዎች መሞታቸው ታውቋል።

በወረዳው በስፋት የተዛመተው ወረርሽኝ ከቁጥጥር ውጪ ከሚሆንበት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን በጉብላክ ከተማ የሚገኘው ጤና ጣቢያ ሌላ አገልግሎት እንዳይሰጥ መከልከሉ ታውቋል።

ሆስፒታሉ ሙሉ በሙሉ በኮሌራ ወረርሽኝ ለተያዙ ሰዎች አገልግሎት እንዲሰጥ በመወሰኑ ሌሎች ታካሚዎች ከፍተኛ ችግር ውስጥ መግባታቸውንም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ለሌላ ህክምና ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡ አዲስ ታካሚዎችን እንደማያስተናግድም ሆስፒታሉ አስታውቋል። በጉብላክ ከተማ ብቻ በወረርሽኙ ሶስት ሰዎች የሞቱ ሲሆን ይህ ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል መረጃዎች ያሳያሉ።

በዳንጉር ወረዳው ግልገል በለስ እስር ቤት የሚገኙ በርካታ እስረኞች በወረርሽኙ በመያዛቸው የተነሳ እስር ቤቱ ለጥየቃ መከለከሉንም ለመረዳት ተችሏል።

ከተፋፈገና ለጤና አስጊ ከሆነ የእስር ቤቱ ይዞታ ጋር ተዳምሮ ወረርሽኙ በስፋት እየተዛመተ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በበሽታው የሞተ እስረኛ ስለመኖሩ የታወቀ ነገር የለም።

ወደ ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ጤና ቢሮ ስልክ በመደወል ስለተከሰተው ወረርሽኝ ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የጉብላክ ከተማ ሆስፒታል የህክምና ባለሙያ ለኢሳት እንደገለጹት የመንግስት ሃላፊዎች ስለወረርሽኙ መረጃ እንዳይወጣ ጥብቅ ቁጥጥር እያደረጉ ነው።

የተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ አይደለም የሚል መከላከያ እንድንሰጥ በሆስፒታሉ ሃላፊዎች እንገደዳለን ብለዋል እኒሁ የህክምና ባለሙያ።

ሆስፒታል ከመጡትና ህይወታቸው ካለፈው በላይ በወረርሽኙ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልም ስጋት እንዳለ ባለሙያው ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በድሬዳዋ በተመሳሳይ የኮሌራ ወረርሽኝ ከ100 በላይ ሰዎች በመታከም ላይ መሆናቸውን ዥንዋ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ከድሬዳዋ በተጨማሪ አዲስአበባና ባህርዳርም የወረርሽኙ ምልክት የታየባቸው መሆኑም ተገልጿል።

መንግስት በሀገሪቱ የኮሌራ ወረርሽኝ አልተከሰተም በሚል እየደበቀ ቢሆንም ዓለም ዓቀፍ ሪፖርቶች የሚያወጧቸው መረጃዎች ወረርሽኙ መከሰቱን በማረጋገጥ ላይ ናቸው።