በባህርዳር ዙሪያ ቦንብ መፈንዳቱን ተከትሎ ውጥረ ሰፍኖ ሰነበተ

ግንቦት ፲፬ ( አሥራ አራት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ባለፈው ቅዳሜ ምሽት በባህርዳር ዙሪያ ወረዳ ጭስ አባይ ከተማ ላይ የእጅ ቦንብ መወርወሩን ተከትሎ ባህርዳር እና አካባቢዋ እስከ ትናንት ድረስ ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ፌደራል ፖሊስ አባላት ተወረው እንደነበር የአይን እማኞች ገልጸዋል።
ለልማት በሚል በሚወሰድ መሬት የካሳ ክፍያ ውዝግብ መነሳቱን የሚገልጹት ምንጮች፣ ማንነታቸው ያልተወቁ ሃይሎች፣ በአካባቢው ነዋሪ የሆነና የህወሃት/ኢህአዴግ የመረጃ ሰው ነው በሚባለው ግለሰብ መኖሪያ ቤት ላይ ቦንብ አፈንድተዋል። ግለሰቡ በአካባቢው ያሉ አገዛዙን የሚቃወሙ አርሶአደሮችን እየጠቆመ እንደሚያሲዝ የተናገሩት ምንጮች፣ በተጠላው ቦንብም ልጁ ቆስሎ በህክምና ላይ ይገኛል። እንዲሁም ባህር ዳር ግንቦት 20 ቀበሌ ክልል ውስጥ ልዩ ስሙ ልደታ ቤተ ክርስቲያን አቅራቢያ አንድ ማንነቱ ለጊዜው ያልታወቀ ግለሰብ ሞቶ ተገኝቷል።
የአይን እማኞች በፎቶ አስደግፈው እንደገለጹት ከቅዳሜ ጀምሮ በባህርዳር የልዮ ኃይል አባላት አራት አራት ሆነው ነው በተለይ ጣና ገበያ ና መናኽሪያ አካባቢ ይዘዋወሩ ነበር።