በባህርዳር ከፍንዳታ ጋር በተየያዘ በጥርጣሬ በተያዙ ሰዎች ላይ የቴሌቪዥን ቀረጻ በመካሄድ ላይ መሆኑ ተገለጸ

ኢሳት (ሚያዚያ 26 ፥ 2009)

ባለፈው ቅዳሜ በባህርዳር ከተከሰተው ፍንዳታ ጋር በተያያዘ በጥርጣሬ በተያዙ ሰዎች ላይ የቴሌቪዥን ቀረጻ በመካሄድ ላይ መሆኑን ምንጮች ለኢሳት ገልጹ። የገዢው ፓርቲ ምርት የሆነውን ባላገሩ ቢራ ለማስተዋወቅ በተጠራ የሙዚቃ ኮንሰርት አካባቢ በተከሰተ ፍንዳታ ፕሮግራሙ መቋረጡ ይታወሳል።

በጥርጣሪ በተያዙት ግለሰቦች ላይ ማክሰኞ የተጀመረው ቀረጻ በአማራ ክልል ቴሌቪዥን አማካኝነት እየተፈጸመ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል። ይህንን ሂደት በበላይነት የሚመሩት የማነ የተባሉ የአካባቢው የኮማንድ ፖስቱ ቃል አቀባይ ሲሆኑ፣ ታሳሪዎቹ በተሰጣቸው ትዕዛዝ መሰረት የተነገራቸውን ግለሰብና ድርጅት ወንጅለው መግለጫ እንደሰጡም መመሪያ ተላልፏል።

በጥርጣሪ የተያዙት ግለሰቦች በጉዳዩ ላይ ፍርድ ቤት ስለመቅረባቸውም የታወቀ ነገር የለም። በግለሰቦቹ ላይ ምርመራው በአጭር ቀናት ተካሄዶ ወዲያውኑ መግለጫ እንዲሰጡ የተደረገበት ምክንያት ግልፅ አልሆነም። አንዳንድ የአካባቢው ምንጮች እንደሚገልጹት ኮማንድ ፖስቱ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የሌላቸውና ለዚሁ ተግባር ያሰለጠናቸውን እየተጠቀመ ሲሆን ይችላል የሚል ግምት ተንጸባርቋል።

በባህር ዳር፣ በተለይም በጎንደር በቅርብ ጊዜ በተደጋጋሚ እየተከሰቱ ካሉ የቦምብ ፍንዳታዎችን ጋር በተያያዘ በጥርጣሬ በርካታ ሰዎች ወዲያዉኑ እየታፈሱ በመታሰር ላይ ቢሆንም፣ ጥቃቱ ቀጥሏል።

የአሜሪካ መንግስትና የብሪታኒያ መንግስት ጉዳዩ አሳስቧቸው ለዜጎቻቸው ማስጠንቀቂያ መስጠታቸው ይታወሳል።

ባለፈው ቅዳሜ ባህር ዳር በመካሄድ ላይ በነበረው የሙዚቃ ኮንሰርት አካባቢ በደረሰው የቦምብ ፍንዳታ ወቅት በመድረክ ላይ ሙዚቃ ስታቀርብ የነበረችው ድምጻዊት ኩኩ ሰብስቤ በድንጋጤ ሙዚቃውን አቋርጣ ከመድረክ ስትወርድ ኮንሰቱም በዚሁ ሳቢያ ተቋርጧል።

በዚሁ መድረክ የሙዚቃ ዝግጅታቸውን ያቀርባሉ ተብለው ስማቸው የተጠቀሱት ሌሎች ሁለት ድምጻውያን አንጋፋው መሃመድ አህመድ ከመነሻው የቀረ ሲሆን፣ አርቲስት አረጋኸው ወራሽም በዝግጅቱ አልተሳተፈም።