በባህርዳር ከተማ የሚገኙ የሃይማኖት አባቶችና የከተማዋ ነዋሪዎች  የታሰሩ ወጣቶች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ  አፈሳውም እንዲቆም ጠየቁ

ነሃሴ  ፮ ( ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከአንድ ቀን በፊት በባህር ዳር ከተማ የሚገኙ የሃይማኖት አባቶችን በመሰብሰብ ሃገሪቱ ሰላማዊ እንድትሆን ህብረተሰቡን እንዲመክሩ ጠይቀዋል፡፡ የሃይማኖት አባቶች ለርዕሰ መስተዳድሩ በሰጡት ምላሽ በተለያየ ጊዜ ህዝቡ የሚያቀርበውን ጥያቄ በይደር ከማቆየት ይልቅ አፋጣኝ የሆነ መልስ መስጠት እንደሚገባ የተናገሩ ሲሆን አሁንም በወልቃይት የአማራ ማንነት ላይ የተነሳውን የህዝብ ጥያቄ በአስቸኳይ ልትመልሱ ይገባል በማለት አሳስበዋል፡፡

የሃይማኖት አባቶች ‹‹ወደ ህዝቡ ወርደን ተው! የምንለው ለተጠየቀው የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ ምላሽ ይዛችሁ ስትጠሩን ብቻ ነው›› በማለት ያልተጨበጠ ነገር በመያዝ ወደ ህዝቡ ሄደው መጋጨት እንደማይፈልጉ ተናግረዋል፡፡

የሃይማኖት አባቶች በ1997 ዓም.የነበረውን የህዝቡንና የመንግሰትን ግጭት አስታውሰው በወቅቱ ‹‹የህዝቡን ማንኛውንም ጥያቄ እንመልሳለን ህዝቡን አረጋጉልን ››ተብለው ጣልቃ እንዲገቡበገዢው መንግሰት ተጠይቀው የማረጋጋት ስራ ቢሰሩም፤ የገዢው መንግስት ግን ምንም ዓይነት የማስተካከያ ርምጃ ሳይወስድ በመቅረቱ በህዝቡ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት እንዳሳጣቸው ተናግረዋል፡፡

የሃይማኖት አባቶች አክለውም ሰሞኑን በጭፍን ሲታፈሱ የነበሩት ልጆቻቸው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡ይህን መፈጸም ህብረተሰቡ ወደ ምሬት በመግባት  የብቀላ እርምጃዎችን እንዳይወስድ ለማድረግ  ትልቅ ጠቀሜታ ስላለው የተባባሰ ነገር ከመፈጠሩ በፊት የክልሉ መንግስት ሊወስድ የሚገባው ዋናው እርምጃ ይህ መሆኑን ተናግረዋል።

በተያያዘ ዜና ትናንት የክልሉ አመራሮች በተለያዩ አዳራሾች የብአዴን ኢህአዴግ አባላትን በማሰባሰብ በወቅታዊ የሃገሪቱ ጉዳይ ላይ አወያይተዋል፡፡የክልል ምክር ቤትን አዳራሽ ጨምሮ በተለያዩ መስሪያ ቤቶችና አዳራሾች  በተካሄዱት ስብሰባዎች የተገኙት አባላት በብአዴን ዝምታ ከፍተኛ ቁጭት ላይ መሆናቸውን ሲገልጹ ተሰምተዋል፡፡

‹‹እንደ ብአዴን ያለብንን ችግር ግለጹልን››ተብሎ የተጠየቀው ተሰብሳቢ‹‹ለመሆኑ ብአዴን የሚባል ፓርቲ አለ ወይ?››በማለት መልሰው የጠየቁ ሲሆን ፣ ህዝቡ በህውሃት መገዛት ይበቃናል ብሎ ሲነሳ አመራሩም የህውሃትን እድሜ ለማስቀጠል ከሚሯሯጥ አብሮ በቃኝ ሊል እንደሚገባው በአንክሮ ተናግረዋል፡፡

‹‹ህዝቡ የህውሃት አገዛዝ በቃኝ ካለ አብራችሁ ልትታገሉና ራሳችሁን ችላችሁ ልትመሩ ይገባል›› በማለት የተናገሩት ተሰብሳቢዎች ፣ ይህን ማድረግ ካልቻሉ ህዝቡ በትግሉ ገፍቶ ራሱን ነጻ እንዲያዎጣ መልቀቅ እንዳለባቸው በአንክሮ ተናግረዋል፡፡

በሁሉም አካባቢ በተሰበሰቡ የፓርቲው አባላት እንደተጠየቀው በሰሞኑ ሰላማዊ ሰልፍ ምክንያት የታሰሩት ከአንድ ሽህ የሚበልጡ ወጣቶች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ እና አሁንም በመሳደድ ላይ ያሉ የከተማዋ ነዋሪዎችን  የክልሉ መንግስት ሊታደጋቸው እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡

በስብሰባው በርካታ ጉዳዮች ተነስተው የብአዴን ችግሮች የተነገሩ ሲሆን በሁሉም የስብሰባ ቦታዎች በተገኙ መረጃዎች የብአዴን አመራሮች ሙሉ በሙሉ ወደ ትግሉ እንዲቀላቀሉና ከህዝብ ጎን በመቆም የህውሃትን ስርዓት ‹‹በቃን!›› እንዲሉ አባላቱ ጥያቄውን  ለአመራሮች አቅርቧል፡፡

በሌላ በኩል በዕሁዱ ሰላማዊ ሰልፍ ተተኩሶባቸው ከባህርዳር ፈለገ ህይወት ሆስፒታል ህክምና ሲሰጣቸው ከነበሩት መካከል ሁለት ወጣቶች ህይወታቸው አልፏል፡፡በትላንትናው እለት ያረፈው የደብረ ማርቆስ ወጣት አስክሬኑ ወደ ደብረ ማርቆስ በመጓዝ የቀብሩ ስነስርዓት ተፈጽሟል፡፡የደብረ ማርቆስ ነዋሪዎች በወጣቱ ሞት የተሰማቸውን ሐዘን በቁጭት እየገለጹ ሲሆን ፣ ሰሞኑን በሚደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ባዶ እጃቸውን በመውጣት በባህርዳር ወጣቶች ላይ የደረሰው ግድያ እንዲከሰት እንደማይፈቅዱ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ በአጋዚ አልሞ ተኳሸች ጭንቅላቱን ተመቶ ሲያጣጥር የሰነበተው ማንነቱ ያልታወቀው ሌላው ወጣትም በዛሬው እለት ህይወቱ አልፏል፡፡ወጣቱ በኪሱ የያዘው ምንም አይነት መታወቂያ ባለመኖሩ ማንነቱ ያልተለየ ሲሆን ምንም ዓይነት ቤተሰብ መጥቶ እንዳልጠየቀው የሆስፒታሉ ሃኪሞች ተናግረዋል፡፡ህይወቱ እስኪያልፍ ድረስ ከሆስፒታሉ ሐኪሞች ኪስ በሚወጣ ገንዘብ ልዩ ልዩ እርዳታ ሲደረግለት የቆየውን ወጣት አስክሬን ለመረከብ የመጣ ቤተሰብ ባለመኖሩ በነገው እለት በከተማ አስተዳደሩ በኩል ግብዓተ መሬቱ ሊከናዎን እንደሚችል ምንጮች ተናግረዋል፡፡