በባህርዳር በሕወሃት አጋዚያን የተጨፈጨፉት ከ50 በላይ ወጣቶች ለማሰብ የተጠራው አድማ በስኬት ተጠናቀቀ

(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 1/2009) በባህርዳር በሕወሃት አጋዚያን የተጨፈጨፉ ከ50 በላይ ወጣቶችን ለመዘከር የተጠራው አድማ በስኬት ተከናወነ።
የንግድ መደብሮች ሲዘጉ፣ተሽከርካሪዎች ደግሞ እንቅስቃሴ ባለማድረግ በግፍ የተገደሉትን የባህርዳር ወጣቶች በሐዘን አስታውሰዋል።
አድማው ሌሎች የተወሰኑ የአማራ ክልል ከተሞችንም አዳርሷል።
የባህርዳር ከንቲባ አቶ አየነው በላይና የከተማዋ ፖሊስ መምሪያ ሃላፊ ኮማንደር ዋለልኝ ዳኘው አድማው መደረጉን አምነው የንግድ ተቋማቱን ለማስከፈትና ተሽከርካሪዎችን ስራ ለማስጀመር የማግባባት ስራ መካሄዱን ገልጸዋል።
የተወሰኑ የንግድ መደብሮችና ሆቴሎች እንዲሁም ተሽከርካሪዎች በሃይል ተገደው ስራ እንዲጀምሩ መደረጋቸውንም ምንጮቻችን ገልጸዋል።
ባህርዳር በአገዛዙ የተፈጁባትን ከ50 በላይ ወጣት ሰማእታቶቿን በሀዘን አስባ ነው የዋለችው።
በከተማዋ የወታደር ግርግር፣ማስፈራሪያውና ዛቻው አይሎ የነበረ ቢሆንም በግፍ ለተገደሉት ወጣቶች ሐዘኑን የነፈገ አልነበረም።-ከተወሰኑ የአገዛዙ ደጋፊዎች በስተቀር።
በባህር ዳር የነሐሴ 1 ሰማእታቱን ለማሰብ የንግድ መደብሮች ዝግ ሆነዋል፣ተሽከርካሪዎች ደግሞ ከእንቅስቃሴ ታቅበው ከተማዋን ጭር አድርገዋት ነው የዋሉት።
በባህርዳር የሰማእታቱን ቀን ምክንያት በማድረግ ሁለት የቦምብ ጥቃቶችም ተፈጽመዋል።
ከፍተኛ ወታደራዊ ጥበቃና የሰራዊት ወረራ በነበረበት የአማራ ክልል ርእሰ ከተማ ባህርዳር የተፈጸሙት ጥቃቶች አንዱ አባይ ማዶ ብአዴን ጽህፈት ቤት አቅራቢያ ነበር።ሌላኛው ደግሞ የአገዛዙ ተላላኪ ነው በተባለ ባለስልጣን ቤት ላይ ከፖሊ ወደ ፔዳ በሚወስደው መንገድ ላይ ተፈጽሟል።
እንዲህ አይነት ሁኔታ ሲፈጠር ብዙ ጊዜ ዝምታን የሚመርጡት የአገዛዙ ባለስልጣናት ስለ ቦምብ ጥቃቶቹ መፈጸም በመግለጫቸው ለመናገር ተገደዋል።
የባህርዳር ፖሊስ መምሪያ ኮማንደር ዋለልኝ ዳኘው ስለሁኔታው ይናገራሉ።
የባህርዳር ከተማ ከንቲባ አቶ አየነው በላይም አድማው መደረጉን አምነው የንግድ መደብሮችን ለማስከፈትና ተሽከርካሪዎችን ስራ ለማስጀመር ቤት ለቤት የማግባባት ስራ መሰራቱን ነው የገለጹት።
እርሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ የአገዛዙ ታጣቂዎች ግን የሃይል እርምጃ ለመውሰድ ተገደዋል።
ሚሊኒየም ካፌን የመሳሰሉት አንዳንድ መደብሮችም በወታደሮች ተከበው እንዲከፍቱ መደረጉ ነው የተገለጸው።ፍሌቨር ጁስ ቤት፣ካሪቡ ካፌ፣ግራንድ ካፌና ዮሞካ ቡና የተባሉት የንግድ ድርጅቶች ግን በፈቃደኝነት የከፈቱና በአድማው አንተባበርም ያሉ መሆናቸውን ምንጮች ገልጸዋል።
እናም ከነዚህ ድርጅቶ ህብረተሰቡ በአገልግሎታቸው ከመጠቀም እንዲቆጠብ የባህርዳር ወጣቶች ጥሪ አቅርበዋል።
የመኪና ሰሌዳ እየዞሩ እስከመፍታትም የሄዱበት ርቀት እንደነበርም መረጃዎች አመልክተዋል።
የባህርዳሩን አድማ በመደገፍ ደብረታቦር፣ወረታ፣ጎንደር፣ወልዲያ፣ዳንግላ፣እንጅባራና በሌሎች የአማራ ክልል ከተሞች ውጥረት ነበር።
የንግድ መደብሮቻቸውንም የዘጉ ነበሩበት።በባህር ዳር በአልሞ ተኳሾች የተገደሉትን ከ50 በላይ ወጣቶችን ለማሰብ የተጠራው አድማ ስኬታማ እንደነበር የከተማዋ ወጣቶች አስተባባሪ ኮሚቴ ለኢሳት ያደረሰው መረጃ ያመለክታል።
ባህርዳር ሰማእታቶቿን በሀዘን አስባለች።ሰማእቱ የሞቱለት የነጻነት አላማም አይረሳም ብለዋል ነጻነት ናፋቂዎቹ የባህርዳር ነዋሪዎች።