በቢሾፍቱ (ደብረዘይት) በአንድ ሆቴል ውስጥ የተወረወረ ቦንብ ጉዳት አደረሰ

ኢሳት (መጋቢት 22 ፥ 2008)

በቢሾፍቱ ወይንም ደብረዘይት ከተማ በዛሬው ዕለት መጋቢት 22/2008 በአንድ ሆቴል ላይ በተወረወረ የእጅ ቦንብ በሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሱ ታወቀ። በቦምቡ በትንሹ አንድ ህጻን መገደሉት የአይን እማኞችና የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

በቢሾፍቱ ጥበቃውም ተጠናክሮ መቀጠሉም ተመልክቷል።

አዋሽ በተባለ ሆቴል ላይ ማንነቱ ባልታወቀ ግለሰብ በተወረወረ የእጅ ቦምብ የሶስት ዓመት ህጻን  የተገደለ ሲሆን፣ የህጻኑ ወላጆችም መቁሰላቸውም ታውቋል።

ከቦንምብ ፍንዳታው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ረቡዕ ዕለት ልብነ-ድንግል በተባለው ት/ቤት ላይ ተኩስ መከፈቱን መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል። ተኳሹ ባይታወቅም አደጋ አለመድረሱ ተመልክቷል።

በአሁኑ ወቅት ቢሾፍቱ በከፍተኛ የጸጥታ ሃይሎች ጥበቃ ውስጥ እንደምትገኝም ለመረዳት ተችሏል።

በቦምብ ሆነ በመሳሪያ ጥቃት ስለፈጸመው ወገን ወይንም ሃይል እስካሁን የተገለጸ ነገር የለም።

ባለፉት አራት ወራት በአዲስ አበባው ታላቁ አንዋር መስጊድ እንዲሁም በተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የቦንብ ፍንዳታ መድረሱ ቢታወቅም፣ በመንግስት በኩል የተሰጠ መገለጫ የለም።

አንዳንድ የውስጥ ምንጮች እንደሚገልጹት፣ ፍንዳታዎቹ ሆን ተብለው የታሰሩ የኦሮሞ አክቲቪስቶችና የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለመወንጀል በቪዲዮ የተደገፈ ቅንብር እየተዘጋጀ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።