በቀድሞው የምርጫ ቦርድ ምክትል ሃላፊ የሚመራው የሰብአዊ መብት ድርጅት በቂሊንጦ የደረሰው የእሳት አደጋ ሆን ተብሎ በእስረኞች የተነሳ ነው አለ

መጋቢት ፳፯ (ሃያ ሰባት)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ራሱን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ብሎ የሚጠራው እና በህወሃት አባሉ በቀድሞው የምርጫ ቦርድ ምክትል ሊ/መንበር ዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚአብሄር የሚመራው ድርጅት በዛሬው ዕለት ለፓርላማው ፍትህ እና አስተዳደር ጉዳዮች ቆሚ ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርት፣ የእሳት አደጋው እንዲነሳ ያደረጉት በከፍተኛ ወንጀል ተጠርጥረው የፍርድ ሂደቱን የሚጠባበቁ እስረኞች ናቸው በማለት የፖሊሲን መረጃ አጠናክሯል።
የኮሚሽኑ ኮምሽነር ዶ/ር አዲሱ ገ/እግዚአብሄር በሪፖርታቸው ከአደጋው ጋር ተያይዞ በጠቅላላው 23 ሰዎች እንደሞቱ በመጥቀስ ከእነዚህ ውስጥ 21 ያህሉ በጭስ ታፍነው መሞታቸውንና 2 ደግሞ ሊያመልጡ ሲሉ መገደላቸውን ገልጸዋል:: በአደጋው የ15 ሚሊየን ብር ንብረት መውደሙንም አስታውቀዋል፡፡ የእስር ቤት ምንጮች ቀደም ብሎ እንደተናገሩት ግን የሟቾች ቁጥር ከዚህ በላይ እንደሆነ፣ አብዛኞቹ እስረኞች ሆን ተብሎ በጠባቂዎች እንዲገደሉ መደረጉንና አደጋውም በቅንብር እንደተነሳ የሚያመለክት ነው።
ዶ/ር አዲሱ አደጋው ከመከሰቱ በፊት በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ረብሻ መፈጠሩንና በእስር ቤቱ መገኘት የሌለባቸው አደንዛዥ እዖች ገብተው መገኘታቸውን ቢገልጹም፣ ከፍተኛ ቁጥጥር በሚደረግበት እስር ቤት ውስጥ አደንዛዥ ዕጹ እንዴት እንደገባ አልገለጹም።ገብቷል ለተባለው አደንዛዥ እጽ ሃላፊነት መውሰድ ያለበት የትኛው አካል እንደሆነም አልተናገሩም።
በቂሊንጦ ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም የደረሰውን ቃጠሎ ተከትሎ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩንና የኢትዮጵያ የአየር ሃይል ባልደረባ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤን ጨምሮ በርካታ እስረኞች ለአደጋው ተጠያቂ ተደርገው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት በመታየት ላይ ነው። 5 የጥበቃ አባላትም እንዲሁ በእስር ላይ ይገኛሉ።