በሽብርተኝነት ተጠርጥረው የተከሠሱት እነ ሉሉ መሰለ የመከላከያ ምስክሮቻቸውን አሰሙ::

ግንቦት ፬ ( አራት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በተመሰረተባቸው የሽብርተኝነት ክስ በፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት እንዲከላከሉ እንዲከላከሉ የተበየነባቸውን የሰማያዊ ፓርቲ አባልና የ2007 ዓ.ም ሀገራዊምርጫ የአርባ ምንጭ አካባቢ የክልል ምክር ቤት ተወዳዳሪ አቶ ሉሉ መሰለን ጨምሮ 7 ተከሳሾች የመከላከያ ምስክሮቻቸውን አሰምተዋል፡፡
አቶ ሉሉ መሰለ የቀረበባቸው ክስ፣በአርባ ምንጭ ከተማ የሚገኙ ወጣቶችን በአርበኞች ግንቦት ሰባት አባልነት በመመልመል ወደ ኤርትራ ይልካል የሚልነው።
ለአቶ ሉሉ በመከላከያ ምስክር ሆኖ የቀረበው ጌታሁን በየነ እንዲሁም ሌሎች ከኤርትራ መጡ የተባሉና በቂሊንጦ በእስር ላይ የሚገኙ ታሳሪዎች ሲሆኑ፤ ሁሉም የአርበኞች ግንቦት ሰባት አባላት እነደሆኑ በመጥቀስ ፣ “ወደ ኤርትራ የሄድነው በራሳችን ፍላጎት እንጂ ሉሉ መልምሎን አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ሌላዋ ሴትተከሳሽ አየለች አበበም እንዲሁ የመከላከያ ምስክሮቿን አቅርባ አሰምታለች፡፡
የቀረቡት የመከላከያ ምስክሮች አየለችመምህር እንደሆነችና በመኖሪያ ቤቷ ተገኘ የተባለው መሳሪያ ውሸት እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡
በምስክርነት የቀረበውና በእስር ላይ የሚገኘው ወንድሟ ወንዶሰን አበበ “እህቴን ሰላም እንድላት ይፈቀድልኝ?” በማለት እምባ እየተናነቀው የጠየቀ ሲሆን፤ በፍርድ ቤቱ ተፈቅዶለት ከእህቱ ጋር ሲገኛኑ የነበረው ሁኔታ በችሎት የነበረውን ታዳሚ ልብ የነካና በእንባ ያራጨ እንደነበር ተመልክቷል። በዚህ የወንጀል መዝገብ ከአንድ ቤተሰብ አባላት ውስጥ ሦስት ሰዎች ታስረዋል።
አቶ በፍቃዱ አበበ ሰባት አመት ተፈርዶበት በዝዋይ እስር ቤት የሚገኝ ሲሆን፤ወንድም ወንዶሰን አበበ በቂሊንጦ፣እህት አየለች አበበ ደግሞ በቃሊቲ እስርቤት በግፍ እስር ላይ ይገኛሉ፡፡
የተከሳሾቹ የ73 ዓመት አዛውንት አባታቸው የመከላከያ ምስክር ሆነው መቅረባቸውም እንዲሁ ታዳሚውን ሲያነጋግር ነበር።
ከዚህም ባሻገር የተከሳሾቹ አራተኛ ወንድማቸው አቶ እንግዳ አበበ አርባ ምንጭ አካባቢ ከአገዛዙ ጋር በነበረ የተኩስ ልውውጥ እንደተሰዋ መነገሩ ብዙዎችን አሳዝኗል።