በሽብርተኝነት ሥም ተከሰው በእስር ሲሰቃዩ ከነበሩ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት መካከል ስድስቱ ነጻ ተባሉ

ሰኔ ፱ ( ዘጠኝ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከሕግ አግባብ ውጪ ተይዘው የሽብር ክስ ቀርቦባቸው ለዓመታት በእስር ቤት ሲሰቃዩ የነበሩት ስድስት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ከቀረበባቸው ክስ ነጻ ተብለው ተለቀዋል።
ከፍተኛው ፍርድ ቤት ሰኔ 9 ቀን 2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት 1ኛ ተከሳሽ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን፣ 4ኛ ተከሳሽ አቶ አወቀ ሞኙ ሆዴ፣ 8ኛ ተከሳሽ አቶ ተስፋዬ ታሪኩ፣ 10ኛ ተከሳሽ አቶ ታፈረ ካሳሁን፣ 13ኛ ተከሳሽ አቶ እንግዳው ባዩ እና 15ኛ ተከሳሽ አቶ አግባው ሰጠኝ ከቀረበባቸው የሽብር ክስ ነጻ ተብለዋል።
በእነ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን የክስ መዝገብ ከተከሰሱት ውስጥ ሰባቱ ተከሳዮች አቶ በላይ ሲሳይ፣ አቶ አንጋው ተገኝ፣ አቶ ቢሆነኝ፣ አቶ አትርሳው፣ አቶ አለባቸው እና አቶ አባይ ዘውዱ የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ ሲል ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጥቷል። ሁሉም ተከሳሾች በወቅቱ ከአሸባሪዎች ጋር በመገናኘት፣ አሸባሪ ለሆነው ከኢሳት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋዜጠኞች ጋር ቃለመጠየቅ በመስጠት የሚል ክስ ቀርቦባቸው ነበር።
በሰሜን ጎንደር የሰማያዊ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የነበረው 15ኛ አቶ አግባው ሰጠኝ ነሐሴ 28 ቀን 2008. ዓ.ም በቂሊንጦ እስር ቤት ለደረሰው የእሳት ቃጠሎ ተጠያቂ ናችሁ ተብለው ከተከሰሱት በመቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ የክስ መዝገብ በመከሰሱ ከቀረበበት የሽብር ክስ ነጻ ቢባልም ከእስር አይፈታም። አቶ አግባው ሰጠኝ ባለፈው ዓመት የጤናው ሁኔታ ሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን እና “ብሄሬ እየተጠቀሰ ማንነቴ ላይ ያነጣጠረ ስድብ ተሰድቤአለሁ። ከቤተሰቤ እና ከሕግ ጠበቃዬ ጋር እንዳልገናኝ ጨለማ ቤት ውስጥ ታስሬያለሁ” በማለት ለፍርድ ቤት አቤቱታ ማቅረቡ ያታወሳል። በተመሳሳይ የሽብር ክስ ቀርቦባቸው ነጻ የተባሉት የልብ ሕክምና ዶክተር የሆኑት ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ከቂሊንጦ ቃጠሎ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ ይገኛሉ።
በሌላ መዝገብ በተከሰሱት እነ አቶ በቀለ ገርባ የክስ መዝግብ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ፍርድ ቤቱ ለሰኔ 15 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋዋጭ የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቷል። በኮማንድ ፖስቱ ከመንገድ ላይ ታግተው ላለፉት ሰባት ወራት በእስር ላይ ሲሰቃዩ የቆዩት ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ እና የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ አመራር የነበረው አቶ ዳንኤል ሺበሺ ክስ ተመስርቶባቸዋል። ሰኔ 9 ቀን 2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት የቀረበባቸውን ክሶች እንዲከላከሉ ለሰኔ 9 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል።