በሸዋ ሮቢት አንድ የእህል ንግድ ድርጅት ተወካይ በነጋዴውና በመንግስት መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ እራሱን ውሀ ውስጥ ወርውሮ መግደሉ ታወቀ

ህዳር 5 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በሰሜን ሸዋ ዞን በሸዋ ሮቢት ከተማ የሚገኙ ታማኝ የኢሳት ምንጮች እንደገለጡት ለሀላፊው ሞት ምክንያት የሆነው በመንግስትና በነጋዴዎች መካከል አለመግባባት በመፈጠሩ ነው።

መንግስት ወደ ውጭ አገር የሚልከው ማሽ እየተባለ የሚጠራው የአበባ እህል መጠን መቀነሱን ተከትሎ፣  በእህል ንግድ ድርጅት አማካኝነት ግዢ እንዲፈጸም መመሪያ ማውጣቱን የገለጡት ምንጮች፣ መመሪያውን ተንተርሶ፣ 14  የአካባቢው ነጋዴዎች 4 ሺ ኩንታል የማሽ እህል ለእህል ንግድ ድርጅት አስረክበው ነበር። ይሁን እንጅ መንግስት በውሉ መሰረት የነጋዴዎችን ገንዘብ በወቅቱ መክፈል ሲገባው ፣ ውሉን በማፍረስ ነጋዴዎች  ገንዘባቸውን የሚያገኙት በሂደት መሆኑን በመግለጡ፣ በነጋዴውና በመንግስት ባለስልጣናት መካከል ከፍተኛ ውዝግብ ተነስቷል ።

ውዝግቡን ተከትሎ  ጣልቃ የገባው አካባቢው ፖሊስ፣  “ነጋዴዎቹ ለመንግስት የሸጡት እህል እንደማይመለስላቸው ፣ ይሁን እንጅ የነጋዴዎች ገንዘብ ሳይከፈል እህሉ ከሸዋ ሮቢት እንደማይወጣ”  ለነጋዴው በመግለጥ ውጥረቱ እንዲረግብ አድርጎ ነበር። የመንግስት ባለስልጣናት ግን ፖሊስ ከነጋዴዎች ጋር ያደረገውን ስምምነት በመጣስ.  ከባድ መኪናዎችን ወደ ከተማው በማስገባት የነጋዴዎች ንብረት በጉልበት እንዲጫን አድርጓል።

ችግሩን ተከትሎ በበላይ አለቆቹ  ኢ ፍትሀዊ አሰራር የተበሳጨው  የወረዳው የእህል ግዢ ሀላፊ ፣ ከአለቆቹና ከነጋዴዎች የሚመጣበትን ግፊት መቋቋም ተስኖት፣ ራሱን  50 ሜትር ከፍታ ካለው ድልድይ ላይ ወርውሮ በመጣል፣ ህይወቱን አጥፍቷል።

አንድ የችግሩ ሰለባ የሆኑ ነጋዴ ለኢሳት እንደገለጡት የወረዳው ሀላፊ በራሱ ላይ የወሰደው እርምጃ፣ በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የፍትህ አሰራር መበላሸት  የሚያሳይ ነው።