በሶማሌ ክልል በድርቁ ሳቢያ ከ40ሺ በላይ የቁም እንስሳት መሞታቸው ታወቀ

ኢሳት (መጋቢት 15 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በመባባስ ላይ ባለው የድርቅ አደጋ በአንድ ዞን ውስጥ ብቻ እስከአሁን ድረስ ከ40ሺ በላይ የቁም እንስሳት መሞታቸውንና ድርቁ ለሰዎች ህይወት ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ።

በክልሉ የሚገኘው የቆራሄ ዞን ካለፈው ሃምሌ ወር ጀምሮ ለድርቅ ተጋልጦ የሚገኝ ሲሆን፣ በዞኑ በእስካሁኑ ቆይታ ከ40ሺ በላይ የቁም እንስሳት መሞታቸው የዞኑ አስተዳደር ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።

ድርቁ በዞኑ እያደረሰ ያለው ጉዳት በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ሊደርስ የሚችለው ጉዳት እየከፋ ሊሄድ እንደሚችል የአካባቢው ነዋሪዎች አሳስበዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ አለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት በሶማሌ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ዞኖች ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ ለሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት ይሆናል ሲሉ ማሳሰባቸው ይታወሳል።

የቆራሄ ዞን ዋና አስተዳደር ተወካይ አቶ አህመድ ያሲን እስካሁን ድረስ ድርቁ ለሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት አለመሆኑን ገልጸዋል።

ይሁንና በመባባስ ላይ ያለው የዞኑ የድርቅ አደጋ በዚሁ ቀጣይ ከሆነ ሊደርስ የሚችለው ጉዳት አስከፊ ሊሆን እንደሚችል ሃላፊው ስጋታቸውን ተናግረዋል።

በተያዘው ሳምንት የካቶሊክ የእርዳታ ድርጅት ተወካዮች ህይወታቸውን ከውሃ እጥረት ለመታደግ የሞከሩ ነዋሪዎች የተበከለ ውሃ በመጠቀማቸው በትንሹ ስድስት ሰዎች ሞተው በርካቶች ለህመም መዳረጋቸውን ይፋ አድርገዋል። በኢትዮጵያ ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ከተጋለጡ 5.6 ሚሊዮን ሰዎች መካከል ወደ ሁለት ሚሊዮን አካባቢ የሚሆኑት በሶማሌ ክልል ያሉ ሰዎች መሆናቸው ታውቋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በበኩሉ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ለድርቁ ጥሪ ወቅታዊ ምላሽ ባለመስጠቱ በተለይ በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል የሰብዓዊ ቀውስ ሊከሰት እንደሚችል አሳስቧል።

የክልሉ እና የፌዴራል መንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው የምግብ እጥረቱ የከፋ ጉዳት እያደረሰ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል። ይሁንና፣ አለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት ለችግሩ ድጋፍ ባለመገኘቱ ምክንያት ተረጂዎች የሚቀርብላቸው ድጋፍ እየቀነሰ ሊሄድ እንደሚችልና ድርቁ አስከፊታችን መስከረም ወር ድረስ ተባብሶ እንደሚቀጥል አሳስበዋል።

በኦሮሚያ፣ አፋር፣ ደቡብና የሶማሌ ክልል ስር በሚገኙ በርካታ ዞኖች ዳግም የተከሰተው የድርቅ አደጋ ወደ 6 ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንዲጋለጡ አድርጓል።

መንግስትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድርቁን ለመታደግ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ እንደሚያስፈልግ ጥሪ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ይሁንና የእርዳታ ጥሪው ከተላለፉ ወራቶች ቢቆጠሩም የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ትኩረት አለመስጠቱ ታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም በሶማሌ ክልል የድርቁ መባባስን ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች የኮሌራ በሽታ ወረርሽኝ መከሰቱን የክልሉ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

ወረርሽኙን ለመከላከል 18 ጊዜያዊ የጤና አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ተቋቁመው ርብርብ በማደረግ ላይ መሆናቸው ተመልክቷል።

አለም አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅቶች ድርቁ ውሃ ወለድ ተላላፊ በሽታዎችን ሊያስከትል ይችላል ሲሉ ማሳሰባቸው ይታወሳል።