በሶማሌ ክልል በሚገኙ 37 ወረዳዎች የኮሌራ ወረርሽኝ መከሰቱን ተመድ ይፋ አደረገ

ኢሳት ( መጋቢት 27 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል ድርቅ ጉዳት እያደረሰባቸው ካሉ 43 ወረዳዎች መካከል በ37ቱ የኮሌራ ወረርሽን መከሰቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይፋ አደረገ።

የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር ሲባል ከተለያዩ የሃገሪቱ ክልሎች የተውጣጡ ወደ 300 አካባቢ የጤና ባለሙያዎች ወደ ወረዳዎች እንዲሰማሩ የተደረገ ሲሆን፣ ችግሩ ለተጎጂዎች ተጨማሪ ስጋት ማሳደሩ ታውቋል።

በክልሉ አጋጥሞ ያለው የምግብና የውሃ እጥረት ለውሃ ወለድ በሽታዎች መዛመት ምክንያት መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

በሶማሌ ክልል ብቻ ወደ ሁለት ሚሊዮን አካባቢ የሚጠጉ ሰዎች በ43 ወረዳዎች ውስጥ ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ተጋልጠው የሚገኙ ሲሆን፣ ለተረጂዎች በቂ የምግብ ድጋፍ ባለመገኘቱ ድርቁ የከፋ ጉዳት እያደረሰው መሆኑን ድርጅቱ አስታውቋል።

የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ተረጂዎች ለቀረበው የእርዳታ ጥያቄ እስካሁን ድረስ የተጠበቀውን ምላሽ ባለመስጠቱ ምክንያት በአራት የሃገሪቱ ክልሎች የተከሰተው አዲስ የድርቅ አደጋ የሰብዓዊ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።

ባለፈው ወር የካቶሊክ የእርዳታ ድርጅት በሶማሌ ክልል ከዚሁ የድርቅ አደጋ ጋር በተያያዘ የተበከለ የግድብ ውሃን የተጠቀሙ ስድስት ሰዎች መሞታቸውንና በርካቶች ለህመም መዳረጋቸውን ይፋ ማድረጉም አይዘነጋም።

በክልሉ ያሉ በርካታ አርብቶ አደሮች የቁምና የቤት እንስሶቻቸውን በድርቁ ሳቢያ ያጡ በመሆኑ የእርዳታ ስራው የሰው ህይወትን ከመታደግ በተጨማሪ ዘላቂ መፍትሄን መመልከት ያለበት እንደሆነ የእርዳታ ድርጅቶች ይገልጻሉ። የክልሉና የፌዴራል ባለስልጣናት በበኩላቸው ድርቁ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት እንዳያደረስ ርብርብ እየተደረገ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በሃገሪቱ በሰብዓዊ እርዳታ ስራ ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው ወርልድ ቪዥን በበኩሉ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሶማሊያ በደቡብ ሱዳንና ኬንያ በድርቅ ምክንያት ወደ 700ሺ አካባቢ ህጻናት ሊሞቱ እንደሚችሉ በቅርቡ ማሳሰቡ የሚታወስ ነው።

በኦሮሚያ፣ አፋር፣ ደቡብና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች ስር በሚገኙ በርካታ ዞኖች ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ 5.6 ሚሊዮን ሰዎች ለአስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እንዲጋለጡ ያደረገ ሲሆን፣ መንግስት ቁጥሩ በማሻቀብ ላይ መሆኑን ሰሞኑን ይፋ አድርጓል።

ይሁንና መረጃው በሚመለከተው ክፍል ከታየ በኋላ ለህዝብ እንደሚገልጽ የአደጋ መመላከያ ኮሚሽን አስታውቋል።

ይኸው የድርቅ አደጋ እስከፊታችን መስከረም ወር ድረስ ቀጣይ እንደሚሆን የተባበሩት መንግስታት ገልጿል።