በሶማሌ ክልል በልዩ ሃይል የተፈጸመው ግድያና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ትኩረት አለመሰጠቱ ተገለጸ

ኢሳት (መጋቢት 28 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል ባለፈው አመት በልዩ ሃይሎች የተፈጸሙ የነዋሪዎች ግድያና የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሃገሪቱ ባለስልጣናት ዘንድ ትኩረት አለመሰጠቱ ስጋት እንዳሳደረበት ሂዩማን ራይትስ ዎች ሃሙስ አስታወቀ።

በክልሉ የተቋቋሙ ልዩ ሃይሎች በሰኔ ወር 2008 አም በምስራቃዊ የክልሉ ግዛት ስር በምትገኘው ያዳማክ ዱባድ መንደር በፈጸሙት ጥቃት 21 ነዋሪዎች ተገድለው በርካቶች ድብደባና እንግልት እንደተፈጸመባቸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው ሪፖርት አብራርቷል።

ድርጊቱ ከተፈጸመ ዘጠኝ ወራቶች ቢያልፉም የአካባቢው ነዋሪዎች በግድያው ዙሪያ ምንም አይነት ምርመራ አለማካሄዱን በመግለፅ ላይ እንደሚገኙ ሂውማን ራይትስ ዎች ከነዋሪዎች ጋር ያደረገውን ቃለምልልስ ዋቢ በማድረግ በሪፖርቱ አመልክቷል።

በጥቃቱ አካላዊ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች በምስል አስደግፎ ያቀረበው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ የመንግስት ባለስልጣናት ድርጊቱን የፈጸሙትን አካላት ተጠያቂ አለማድረጋቸው ስጋት እንዳሳደረበት ገልጿል።

በመንደሩ ነዋሪዎችና በጸጥታ አካላት መካከል የተፈጠረን አለመግባባት ተከትሎ ልዩ ሃይሎች በወሰዱት የጅምላ እርምጃ 14 ወንዶች እና 7 ሴቶች መገደላቸውን ከድርጅቱ ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል።

የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ በፌዴራል መንግስት ልዩ ትዕዛዝ ከሰባት አመት በፊት መቋቋሙን ያወሳው ሂውማን ራይትስ ዎች፣ በመንደሩ ነዋሪዎች ላይ ግድያን የፈጸሙት የጸጥታ አባላት መኖሪያ ቤቶችና ሱቆች ላይ ዝርፊያ መፈጸማቸውንም አመልክቷል። የጅምላ ግድያው ከተፈጸመ ወራቶች ቢቆጠሩምም መንግስት ድርጊቱን የፈጸሙ አካላትን ለፍትህ ለማቅረብ የወሰደው ተነሳሽነት የለም ሲሉ የሂውማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ የሰብዓዊ መብቶች ተመራማሪ የሆኑት ፊሊክስ ሆርን ገልጸዋል።

በመንግስት ችላ የተባለው ይኸው የንጹህን ሰዎች ግድያ በገለልተኛ አካል ማጣራት እንዲካሄድበት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ጥሪን አቅርቧል።

ተጠሪነታቸው ለክልሉ አስተዳደር የሆኑት ልዩ የፖሊስ አባላት በተለያዩ ጊዜያት የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) ደጋፊዎችና አባላት ናቸው ባሏቸው ነዋሪዎች ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጽሙ መቆየታቸውን በርካታ አካላት ሲገልጹ ቆይተዋል።

በአካባቢው ያለው የጸጥታ ሁኔታ መሻሻል ባለማሳየቱ ምክንያት በርካታ ነዋሪዎች ወደ ጎረቤት ሶማሊላንድ መሰደዳቸውን ሂማን ራይትስ ዎች በሪፖርቱ አስፍሯል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ባለፈው አመት በኦሮሚያ ክልል ለአመት ከዘለቀው ህዝባዊ አመፅ ጋር በተገናኘ የሞቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ግድያ በገለልተኛ አካል መጣራት እንዲካሄድበት አለም አቀፍ ጥሪ ማቅረቡ የሚታወስ ነው።

ይሁንና የመንግስት ባለስልጣናት ከተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጭምር የቀረበውን ጥያቄ ሳይቀበሉት ቀርተዋል።