በሶማሌ ክልል ለምግብ እርዳታ የተጋለጡ ዜጎች ቁጥር 1.7 ሚሊዮን መድረሱን ተመድ ገለጸ

ኢሳት (የካቲት 13 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል አዲስ የተከሰተው የድርቅ አደጋ እየተባባሰ በመሄድ ላይ መሆኑንና ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ የተጋለጡ ሰዎች ቁጥር ወደ 1.7 ሚሊዮን አካባቢ መድረሱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ።

ድርቁ እያደረሰ ባለው ጉዳት ከመኖሪያ ቀያቸው የሚፈናቀሉ አጠቃላይ ሰዎች ቁጥር ወደ 168 ሺ ከፍ ያለ ሲሆን፣ በተለይ በኢትዮጵያ የሶማሊ ክልል ጉዳት እያደረሰ ያለው ይኸው የድርቅ አደጋ ስጋት እያሳደረ መምጣቱን ድርጅቱ ገልጿል።

በሺዎች የሚቆጠሩ የቤት እንስሳት ባለፉት ጥቂት ወራቶች በሞቱበት በዚሁ የሶማሌ ክልል በቀጣዩ ወር ይጥላል ተብሎ የሚጠበቀው ዝናብ ሊኖር እንደማይችል የሜትሪዮሎጂ ትንበያ መኖሩም ተመልክቷል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በበኩሉ ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ የተጋለጡ ሰዎች ቁጥር በቀጣዩ ወር በከፍተኛ ቁጥር በመጨመር በአካባቢው የከፋ የምግብ እጥረትና ጉዳት ሊደርስ እንደሚችል አሳስቧል። የክልሉ መንግስት በበኩሉ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት አፋጣኝ ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረቡን ከሃገር ቤት የተገኘ መርጃ አመልክቷል።

በኦሮሚያ፣ አፋርና የደቡብ ክልሎች ስር በሚገኙ በርካታ ዞኖች አዲስ በተከሰተው የድርቅ አደጋ 5.6 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ተጋልጠው የሚገኙ ሲሆን፣ ወደ 2.4 ሚሊዮን የሚሆኑት በሶማሌ ክልል ብቻ መሆኑ ታውቋል።

በሶማሌ ክልል ካሉ 93 ወረዳዎች መካከል በ67ቱ የድርቅ አደጋ ጉዳትን እያደረሰ እንደሚገኝ የክልሉ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ቢሮ ሃላፊ አቶ አንዋር አሊ ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

በአራቱ ክልሎች ስር በሚገኙ በርካታ ዞኖች ተከስቶ ባለው በዚሁ የድርቅ አደጋ ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ህጻናት ቁጥር በመጨመር ላይ ሲሆን እስከ ታህሳስ ወር ድርስ ብቻ 600 ት/ቤቶች መዘጋታቸው ታውቋል።

ድርቁ በቀጣይ ወራቶች እንደሚቀጥል ትንበያ በመኖሩ የፌዴራልና የክልሉ መንግስት ለተረጂዎች የምግብ አቅርቦትን ለማድረግ ጥረት እያደረጉ መሆኑን የሶማሌ ክልል የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ቢሮ አክሎ ገልጿል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በበኩሉ 5.6 ሚሊዮን ለሚሆኑ ተረጂዎች ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ በድጋሚ አስታውቋል።

መንግስት በበኩሉ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ለቀረበው የእርዳታ ጥያቄ ምላሽን እንዲሰጥ በመጠየቅ ለተረጂዎች የምግብ ድጋፍ ለማድረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጿል። በጎረቤት ደቡብ ሱዳን በተከሰተ ተመሳሳይ የድርቅ አደጋ በሁለት የሃገሪቱ ግዛቶች ረሃብ መከሰቱን ሰኞ ተመድ ይፋ አድርጓል።