በሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ በደረሰ ከባድ የቦንብ ጥቃት ከ300 በላይ ሰዎች ሞቱ

(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 6/2010) በሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ በደረሰ ከባድ የቦንብ ጥቃት ከ300 በላይ ሰዎች ሲሞቱ ከ300 በላይ የሚሆኑ ደግሞ መቁሰላቸው ተሰማ።

የሟቾቹ ቁጥር ከዚህም በላይ ሊጨምር እንደሚችል እየተነገረ ነው።ከአደጋው ጋር በተያያዘ 70 ያህል ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም።

አደጋው አልሻባብ ጥቃት መፈጸም ከጀመረበት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2007 ወዲህ የተፈጸመ በአይነቱ አስከፊ የተባለ የቦንብ ጥቃት ነው ተብሏል።

እስካሁን ስለቦንም ጥቃቱ ሃላፊነትን የወሰደ አካል ባይኖርም የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ግን ሃላፊነቱ የአልሻባብ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ለአልቃይዳ ታማኝነቱን ሰጥቶ የሽብር ጥቃት እየፈጸመ ያለው አልሻባብ ከዚህ በፊት ለደረሱ የቦምብ ጥቃቶች ወዲያውኑ ነበር ሃላፊነትን የሚወስደው።

ፍንዳታው በጣም ህዝብ በሚበዛበት እንዲሁም ሆቴሎች፣ምግብ ቤቶችና የመንግስት ቢሮዎች በብዛት በሚገኙበት አካባቢ መፈጸሙ ጉዳቱን የከፋ አድርጎታል።

የሞቃዲሾ ነዋሪዎች አልሻባብን በማውገዝ እሁድ ሰልፍ የወጡ ሲሆን ከሟቾቹ ውስጥም 111 የሚሆኑት በቤተሰባቸው ተለይተው ወዲያውኑ የቀብር ስነስርአታቸው ተፈጽሟል።

165 የሚሆኑትን አስከሬኖች ማንነት መለየት ባለመቻሉም በጋራ የቀብር ስነስርአታቸው በመንግስት እንደሚፈጸም ቢቢሲ ዘግቧል።

በስፍራው የነበረ በሶማሊያ የቢቢሲ ሪፖርተር እንደዘገበው ሳፋሪ የተባለው ሆቴል ሲደረመስ በውስጡ ያሉ ሰዎች በፍርስራሹ ተቀብረዋል ብሏል።

ሲ ኤን ኤን የሶማሊያ ማስታወቂያ ሚኒስቴርን ጠቅሶ እንደዘገበው ወደ 300 የሚጠጉ ቁስለኞች በሆስፒታል ይገኛሉ።70 ያህል ሰዎች ደግሞ የደረሱበት አልታወቀም።

ሰዎችን ከፍርስራሹ ውስጥ የማውጣቱ ስራ መቀጠሉንና ከዚህም ጋር በተያያዘ የተጎጂዎችና የሟቾች ቁጥር እያሻቀበ ሊሄድ እንደሚችል እየተነገረ ነው።

40 የሚሆኑ ቁስለኞች ጉዳታቸው ከፍተኛ በመሆኑ ለህክምና ወደ ቱርክ ለመጓዝ በአየር ማረፊያ በመጠባበቅ ላይ ወደሚገኘው የቱርክ የወታደራዊ አውሮፕላን ተወስደዋል።
አውሮፕላኑ የሕክምና እርዳታ ይዞ መምጣቱም ተዘግቧል።

የመጀመሪያው ፍንዳታ የሳፋሪ ሆቴልን ሲያፈራርስ በአቅራቢያው በሚገኘው የኳታር ኤምባሲም ላይ ጉዳት አድርሷል። የኤምባሲው ጉዳይ አስፈጻሚም መጠነኛ ጉዳት እንደደረሰበት ታውቋል።

በሁለት ተሽከርካሪዎች ላይ በተጠመደ ቦምብ የደረሰው ፍንዳታ እስካሁን በሞቃዲሾ ከደረሱት ፍንዳታዎች አስከፊው ነው ተብሏል።

ፖሊስ ፈንጂ ስለጫነ ተሽከርካሪ አስቀድሞ መረጃው ደርሶት እየተከታተለ እንደነበር የሞቃዲሾ ፖሊስ አዛዥ ኮለኔል አህመድ ሀሰን ተናግረዋል።

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት በሀገሪቱ የሶስት ቀን ሀዘን ሲያውጁ ባንዲራም በግማሽ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ታዟል።