በሳውዲ አረቢያ ህጋዊ ፈቃድ የላችሁም ተብለው እንዲወጡ ከተጠየቁት መካከል አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ተነገረ

ኢሳት (ሚያዚያ 24 ፥ 2009)

የሳውዲ አረቢያ መንግስት ህጋዊ ፈቃድ የላቸውም በሚል በ90 ቀናት ውስጥ ሃገሪቱን ለቀው እንዲወጡ በማድረግ ላይ ካሉት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ተገለጠ።

የሳውዲ መንግስት ባለፈው ወር ተግባራዊ ባደረገው በዚሁ አዲስ መመሪያ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ የተለያዩ ሃገራት ዜጎች ሃገሪቱን ለቀው ይወጣሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ከ300 ሺ የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ማይግራንትስ ራይትስ (Migrants’ Rights) የተሰኘ አለም አቀፍ ተቋም አስታውቋል።

አዲሱ መመሪያ ተግባራዊ ከተደረገ 30 ቀናት ቢሞሉትም እስከ አሁን ድረስ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱ ሰዎች ቁጥር ከአራት ሺ በታች መሆኑን መንግስት ገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መመሪያው ተግባራዊ ከመደረጉ ጀምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ኢትዮጵያውያን ከሃገሪቱ እንዲወጡ ቢያሳስብም፣ መመለስ የቻሉት ሰዎች ቁጥር ከተጠበቀው በታች መሆኑ ታውቋል።

የፊሊፒንስ፣ ህንድ፣ ሲሪላንካ፣ የናይጀሪያና የሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ዜጎች የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ሳይጠናቀቅ ከሃገሪቱ በብዛት በመውጣት ላይ መሆናቸው ተመልክቷል።

ይሁንና፣ ሳውዲ አረቢያ ለሁለተኛ ጊዜ ያወጣችው ከሃገር ውጡ መመሪያ ከሚመለከታቸው ሰዎች መካከል ወደ ኢትዮጵያ የሚመለሱት ቁጥር በጣም አነስተኛ መሆኑ ታውቋል።

ሃገሪቱ ከሁለት አመት በፊት ተግባራዊ ያደረገቸው ተመሳሳይ መመሪያ ተከትሎ ከ150 ሺ የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገር መመለሳቸው የሚታወስ ነው።

የአለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት እና ሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ተመላሽ ኢትዮጵያውያንን ለመደገፍ ዝግጅት ቢያደርጉም የተጠበቀውን ያህል ሰው ወደ ሃገር አለመመለሱን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

የሳውዲ አረቢያ መንግስት ከሃገሪቱ እንዲወጡ የጠየቃቸው ሰዎች በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ከወጡ ምህረት እንደሚደረግላቸውና ተመልሶ ወደ ሃገሪቱ የመግባት ዕድል እንደሚኖራቸው ሲገልጽ ቆይቷል።

ይሁንና የጊዜ ገደቡን ተጠቅመው ከሃገሪቱ የማይወጡ የተለያዩ ሃገራት ዜጎች የምህረት ጊዜው ካበቃ በኋላ የእጅ አሻራ እንዲሰጡ እየተደረገ በሃይል እንዲወጡ እንደሚደረግ በመግለጽ ላይ ነው።

የተለያዩ ሃገራት ዜጎቻቸው በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ከሳውዲ አረቢያ እንዲወጡ በማድረግ ላይ ሲሆኑ ከ300ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገር ለመመለስ ሲደረግ የቆየው ዘመቻ ግን የተጠበቀውን ያህል ውጤን እንዳላስገኘ ተመልከቷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለስልጣናት በበኩላቸው በሳውዲ አረቢያ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኢምባሲና ቆንስላል ጽ/ቤቶች ኢትዮጵያውያን በጊዜ ገደቡ ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።