በሲዳማ ዞን ጭኮ ወረዳ መምህራን ለአባይ ግድብ አናዋጣም በማለታቸው ደሞዛቸው ታገደ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 29/2010) በሲዳማ ዞን ጭኮ ወረዳ መምህራን ለአባይ ግድብ አናዋጣም በማለታቸው ደሞዛቸው መታገዱ ተሰማ።

የአባይ ዋንጫ በዙር ጭኮ ወረዳ መግባቱን ተከትሎ እያንዳንዱ የመንግስት ሰራተኛ ከደመወዙ ከ300 ብር ጀምሮ እንዲያዋጣ መመሪያ ተወስኖበታል።

የሴክተር መስሪያ ቤቶች ያለፈቃዳቸው እንደተስማሙ ተደርጎ የተቆረጠባቸው ሲሆን መምህራን ተቃውሞ በማንሳታቸው የመስከረም ወር ደሞዝ ሳይከፈላቸው አራት ቀናት መቆጠሩን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

መምህራኑ ደሞዛችን ካልተከፈለን አንሰራም በማለት ዛሬ ስራ አቁመው መዋላቸው ታውቋል።

የአባይ ዋንጫ ሲዳማ ሲደርስ የፈጠረው ስሜት የደስታ አልነበረም። አብሮት የመጣውና የነዋሪውን ኪስ የሚያራቁት መዋጮም ጭምር በመሆኑ አብዛኛው ሰው ቅሬታ እያሰማ ነው።

በተደጋጋሚ የአባይ መዋጮ የተሰላቸው ህዝቡ ቀድሞ ያዋጣው ገንዘብ ሳይመለስለት ሌላ ዙር ሲጠየቅ ዝምታን አልመረጠም። በተለይ መምህራን።

በሲዳማ ዞን የጭኮ ወረዳ መምህራን ዛሬ ስራ አልገቡም። ደሞዝ ሳይከፈላቸው አራተኛው ቀን አልፏል። ከኑሮ ሽክም መክበድ ጋር ተያይዞ እያንዳንዷን ዕለት ለመሻገር ከባድ የሆነባቸው መምህራን ደሞዝ ሳይከፈላቸው ቀናት ማለፋቸውን በመቃወም ከዛሬ ጀምሮ ስራ ማቆማቸውን አስታውቀዋል።

የኢሳት የመረጃ ምንጮች እንደገለጹት የጭኮ ወረዳ መምህራን ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱበት ምክንያትም ይህው የደሞዛቸው መታገድ ነው።

የአባይ ግድብ ዋንጫ በጭኮ ወረዳ መድረሱን ተከትሎ መምህራን መዋጮውን አንከፍልም ማለታቸው የመንግስት ሃላፊዎችን ያስደሰት አልነበረም።

ከፌደራል የአባይ ግድብ አስተባባሪ ምክር ቤት የተጣለባቸውን የመዋጮ ገንዘብ ማቅረብ ስለሚጠበቅባቸው በውዴታም ይሁን በግዴታ ከደሞዝ ተቆርጦ ገንዘቡ መላክ እንዳለበት ያመኑት የወረዳው ሃላፊዎች ይህንን እቅዳቸውን ለሁለም የመንግስት መስሪያ ቤቶች ያስታውቃሉ።

የተስማማ ባይኖርም ከየሴክተር መስሪያ ቤቱ ከእያንዳንዱ ሰራተኛ ከ300 ብር ጀምሮ እንደሚቆረጥ ተገለጸ።

ይህንን ውሳኔ ለመምህራን የሚቀበሉት አልነበረም። በአዲስ አሰራር መሰረት መምህራን ደሞዝ የሚሰጣቸው ወር በገባ በ25ኛው ቀን ነው። ሆኖም በአባይ ግድብ መዋጮ ላይ ተቃውሞ በማቅረባቸው ደሞዛቸው መታገዱ ነው የተገለጻለቸው።

መምህራን እንደሚሉት ከዚህ ቀደም ከደሞዛቸው እየተቆረጠ የተወሰደባቸው ገንዘብ አልተመለሰላቸውም።

ከዓመት በላይ ለግድቡ እየተቆረጠ የተወሰደባቸው ገንዘብ በገቢያቸው ላይ ከፍተኛ ችግር በመፍጠሩ ኑሮ ከብዷቸው እንደከረሙ የገለጹት መምህራን ዘንድሮም ለአባይ ግድብ እንዴት አዋጡ እንባላለን የሚል ተቃውሞ ማሰማታቸውን ነው የኢሳት ምንጮች የገለጹት።

ሰሞኑን የግድቡ ዋንጫ ወደ ሲዳማ ዞን መግባቱን ተከትሎ ከ23 ወረዳና ከተማ አስተዳደሮች ገንዘብ በስጦታ ማሰባሰብ መጀመሩን የጠቀሱት ምንጮች ከእያንዳንዱ አርሶአደር 50ብር በግድ እየተሰበሰበ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የጭኮ ወረዳ መምህራን በመዋጮው ላይ አንስማማም በማለታቸው የታገደው ደሞዛቸው ካልተሰጣቸው የመማር ማስተማሩን ሂደት እንደሚያቋርጡ በመግለጽ ከዛሬ ጀምሮ ስራ ማቆማቸው የታወቀ ሲሆን ይህንንም እስከ ወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት ድረስ በመሄድ ማሳወቃቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የወረዳው ትምህርት ቢሮ ጽ/ቤትም የበላይ ትዕዛዝ በመሆኑ ምንም ማድረግ አልችልም ማለቱ ተገልጿል።

መምህራኑ በአስገዳጅነት ከደሞዛቸው የሚቆረጥ ከሆነ የጀመሩትን የስራ ማቆም አድማ እንደሚቀጥሉበት መስማማታቸውንም ለማወቅ ተችሏል።

የአባይ ግድብ ግንባታ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ስራው የቆመ ሲሆን ባለፈው ሳምንት ከ2ሺህ በላይ ሰራተኞች መቀነሳቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው።