በሱዳን 4 ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ጉዳት ደረሰባቸው

ግንቦት ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በሱዳን ካርቱም ዉስጥ ሶባ ተብሎ በሚጠራዉ ኢትዮጵያዉያን የሚታሰሩበት ቦታ 4 ኢትዮጵያዉያን በፖሊስ ከባድ ድብደባ ደርሶባቸዋል።። ድብደባው ከመብዛቱ የተነሳ 3ቱ ሰዉነታቸዉ ድብደባዉን መቋቋም ተስኖት ራሳቸውን ስተው  ሃዋዲስ በሚባለዉ ሆስፒታል ተኝተዋልል።። የቀረዉ 1 ደግሞ ወደ ሆስፒታሉ ሳይደርስ በእስርቤቱ ዉስጥ ሳለ ህይወቱን ማለፉን ምንጮች ገልጠዋል።።

በሱዳን የሚገኝዉ ኢትዮጵያዊ ዜጋ እንደ ቆሻሻና እንደ አህያ እየታደነ መታፈስ ከጀመረ የቆየ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ግን በበለጠ እየከፈ መጥቷዋል ይላሉ ኢትዮጵያኑ ። በካርቱም  ፖሊሶች ሃበሾችን ካዩ እንደቆሻሻ ወደ መኪና መጫን የእለት ስራቸዉን አድርገዉታል የሚሉት ምንጮች፣  በተለይ ሳህፋ ዘለጥ፣  ሳሕፋ ሸሪክ፣  ጅሬፍ፣ አርከዊት እና ጀብራ በተባሉት ቦታዎች ፖሊሶች ገንዘብ ሲፈልጉ ሃበሻን እያባረሩ ማሳደደ ነዉ ሲሉ ያክላሉ።

በአጥበራ እና በመደኒ በሚባሉት ቦታዎች በርካታ ኢትዮጵያዉያን ኤድስእና የተለያዩ በሽታዎች አለባቸው እየተባሉ እንደሚታሰሩና ከእስር መዉጣት የሚችሉት ገንዘብ ሲከፍሉ ብቻ መሆኑን ይናገራሉ። ገንዘብ መክፈል ያልቻሉት ደግሞ   ንብረታቸዉንና ገንዘባቸዉን ሳይዙ ከመንገድ እንደታፈሱ  ከእስር ቤት በለሊት ወደ መተማ ተወስደዉ ይወረወራሉ ሲሉ ኢትዮጵያውያን ይገልጣሉ። የኢትዮጵያ መንግስት ከሱዳን አቻው ጋር ወንጀል ሰርተዋል ተብለው የተፈረጁትን አሳልፎ ለመስጠት ስምምነት ላይ ከደረሱ በሁዋላ በስደተኞች ላይ የሚደርሰው ግፍ እንደጨመረ ታውቋል።

በሌላ ዜና ደግሞ ኢትዮጵያ ከሱዳን ነዳጅ ማስገባቱዋን አቁማለች። ሰንደቅ የኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅትን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ኢትዮጵያ ከሱዳን ነዳጅ ማስገባት ያቆመችው፤በሱዳን እና በደቡብ ሱዳን መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ የሱዳን የነዳጅ ኤክስፖርት እክል ስለገጠመው  ነው።

ኢትዮጵያ  ከ 10 ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ የቤንዚን ምርትን ከካርቱም ነዳጅ ማጣሪያ በመረከብ ወደ ሀገር ውስጥ ስታስገባ ቆይታለች።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን  በሁለቱ ሱዳኖች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ የሱዳን የነዳጅ አቅርቦት እክል ስለገጠመው ኢትዮጵያ ከያዝነው ግንቦት ወር 2004 ዓ.ም ጀምሮ ከሱዳን የምታስገባውን ነዳጅ ሙሉ በሙሉ ያቋረጠች መሆኑ ተውቋል

በአሁኑ ሰዓት ነዳጅ ሙሉ በሙሉ በጅቡቲ በኩል የሚገባ በመሆኑ የሀገር ውስጥ የዋጋ ማስተካከያዎች  እንደሚደረጉ የጠቀሱት የድርጅቱ  የነዳጅ ግዥ የሥራ ሂደት መሪ አቶ አባይነህ አወል ፤በምስራቅ የሀገሪቱ ክልል የተወሰነ የዋጋ ቅናሽ ፤ በአንፃሩ መተማና ጐንደር አካባቢን ጨምሮ በሰሜኑ አካባቢዎች የነዳጅ  ዋጋ ጭማሪ ሊደረግ  እንደሚችል አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ 80 በመቶ የሚሆነውን የቤንዚን ፍላጐቷን የምትሸፍነው ከሱዳን በማስመጣት የነበረ ሲሆን፤ ይህን ቤንዚን ለኢትዮጵያ በማቅረቡ በኩል ብቸኛ አቅራቢ የነበረው ‘ሱዳን ፔትሮሊየም  ኮርፖሬሽን’ የተባለ የሱዳን መንግስታዊ ኩባንያ ነበር።

ይህም ሱዳን ካላት መልክዓ ምድራዊ ቀረቤታ አንፃር ሀገሪቱ ለትራንስፖርት ታወጣ የነበረውን ሰባት ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ወጪ ማዳን እንዳስቻለ መረጃዎች ያሳያሉ።

በአሁኑ ጊዜ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ከነዳጅ ቱቦ የአገልግሎት ክፍያ ጋር በተያያዘ በመካከላቸው አለመግባባት መፈጠሩን ተከትሎ በሱዳን አድርጐ ለኤክስፖርት የሚቀርበው የደቡብ ሱዳን ነዳጅ ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል።

ከዚህም ባሻገር በሁለቱ ሱዳኖች መካከል ከ ዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ የመጣው ፍጥጫና ግጭት፤  ኬንያ፣ደቡብ ሱዳን እና ኢትዮጵያ የ አልበሽርን መንግስት በማግለል በጋራ የጀመሩትን የጁባ ፕሮጀክት በጅምሩ እንደሚቀጨው አስተያዬቶች ይሰነዘራሉ።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide