በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ፊት ለፊት ሰላማዊ ሰልፍ ካደረጉ ኢትዮጵያውያን መካከል 500 ሲታሰሩ 65ቱ በግርፋት እንዲቀጡ ተወሰነ

ኢሳት (የካቲት 13 ፥ 2009)

በሱዳን ካርቱም በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሰላማዊ ሰልፍ በማካሄድ የሃገሪቱ መንግስት በመኖሪያ ፈቃድ ላይ የጨምረውን ክፍያ እንዲያሻሽል ጥያቄ ካቀረቡ ኢትዮጵያውያን መካከል 500 አካባቢ የሚሆኑት መታሰራቸውን የሱዳን መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ። 65ቱ ኢትዮጵያውያን እያንዳንዳቸው ህዝብ  በተሰበሰበት 40 ጅራፍ እንዲቀጡም ፍርድ ቤቱ ወስኗል።

ከታሳሪዎቹ መካከል 65ቱ በ40 ግርፋት እንዲቀጡ በመዲናይቱ ካርቱም የሚገኝ ፍርድ ቤት ብይን መስጠቱን ራዲያ ዳባንጋ የተሰኘ የሬድዮ ጣቢያ በጉዳዩ ዙሪያ በቀረበው ሪፖርት አመልክቷል።

የሱዳን መንግስት በቅርቡ 46 የአሜሪካን ዶላር አካባቢ ሲያስከፍል የነበረውን የመኖሪያ ፈቃድ ክፍያ ወደ 308 ዶላር ከፍ ማድረጉ ታውቋል።

ይህንኑ ክፍያ በካርቱም የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ማግባባት እንዲያደርግላቸው ለመጠየቅ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከቀናት በፊት ሰላማዊ ሰልፍ ቢያካሄዱም የኤምባሲው ሰልፍ ከአቅም በላይ ነው በማለት ለሱዳን መንግስት የጸጥታ ሃይሎች ጥሪ ማቅረቡን ለመረዳት ተችሏል።

ጥሪውን ተከትሎ በቦታው የደረሱ የሃገሪቱ የጸጥታ ሃይሎች ወደ 500 የሚሆኑት ለእስር መዳረጋቸን ሬዲዮ ጣቢያው ዘግቧል።

ለእስር ከተዳረጉት ኢትዮጵያውያን መካከል በኤል-ታታ ቀጠና ስር የሚገኘው የኤምቲዳድ ኤል-ዳራጃ ፍርድ ቤት 65ቱ ኢትዮጵያውያን በ40 የጅራፍ ግርፋት እንዲፈጸምባቸው ብይን አስተላልፏል።

65ቱ ኢትዮጵያውያን ከግርፋቱ በተጨማሪ የ771 የአሜሪካን ዶላር ቅጣት የተጣለባቸው ሲሆን፣ ክፍያን መፈጸም ካልቻሉ የሁለት ወር የእስር ቅጣት እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ ወስኗል። በተያዘው ወር መጀመሪያ በካርቱም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሱዳን መንግስት በስደተኞች ላይ ይፈጸማል ያሉትን እንዲሁም የኤምባሲ ትብብር አያደርግልንም ያሉትን ድርጊት በማውገዝ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ አካሄድው እንደነበር ራዲዮ ጣቢያው አክሎ አቅርቧል።

ሱዳን የተለያዩ ወንጀሎችን በሚፈጸሙ የሃገሪቱ ዜጎች ላይ የጅራፍ ግርፊያ ቅጣትን የምታስተላልፍ ሲሆን፣ ይኸው ቅጣት ህዝብ በተሰበሰበት አደባባይ የሚፈጸም መሆኑ ታውቋል። በኢትዮጵያውያኑ ላይ የተላለፈው ይኸው ቅጣት መቼ ተፈጻሚ እንደሚሆን የተገለጸ ነገር የለም።

ከጥቂት አመታት በፊት በሱዳን ካርቱም እንዲሁም በጎረቤት ደቡብ ሱዳን ጁባ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሃገሪቱ ያሉ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ትብብር በምንፈልግ ጊዜ አያስተናግዱንም በማለት ተቃውሞን ሲያቀርቡ አቆየታቸው ይታወሳል።

እነዚሁ ኢትዮጵያውያን ለመንግስት ቅርበት ያላቸውና አካላት እየተለዩ የሚፈልጉት ድጋፍና ትብብር እንደሚደረግላቸው ሲገልጹ የቆዩ ሲሆን፣ በሳውዲ አረቢያና ሌሎች ጎረቤት ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም ተመሳሳይ ቅሬታን ሲያቀርቡ ቆይተዋል።