በሰሜን ጎንደር የነጻነት ታጋዮች የሚፈጽሙት ጥቃት ቀጥሎአል

ሚያዝያ ፲፫ (አሥራ ሦስት) ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአርበኞች ግንቦት7 አባላት የሆኑ ታጋዮች በደምቢያ ወረዳ ሰረባ መስኖ አጠገብ ሌሊት ላይ ጥቃት ፈጽመው፣ 2 ገልባጭ መኪኖችና አንድ እስካቫተር መኪና የተቃጠሉ ሲሆን፣ በታጋዮች እና ድርጅቱን በሚጠብቁት መካከል ለ30 ደቂቃ ያክል የተኩስ ልውውጥ መካሄዱንና አንድ ወታደር መገደሉን ድርጅቱ ለኢሳት በላከው መረጃ አስታውቋል።
ኢሳት ወደ አካባቢው ነዋሪዎች ስልክ በመደወል በመኪኖች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ሲያረጋግጥ፣ በሰው ህይወት ላይ ስለደረሰው ጉዳት ግን ማረጋገጫ ሊያገኝ አልቻለም። የአይን እማኞች ጉራምባ ቀበሌ ላይ በተለይም በቀበሌው ሊቀመንበር አቶ መንግስቱ መኖሪያ ቤት አካባቢ ከፍተኛ የተኩስ ለውውጥ መካሄዱን ገልጸዋል። አካባቢው በወታደሮች ቁጥጥር ስር በመውደቁ የተቃጠሉትን መኪኖች ብዛት በትክክል ለማወቅ እንዳልቻሉ፣ ነገር ግን 3 መኪኖች ጠዋት ላይ ተቃጥለው ማየታቸውን ተናግረዋል። ወደ አካባቢው የተንቀሳቀሱት ወታደሮች የአካባቢው ሚሊሺያ እርምጃ ባለመውሰዱ መሳሪያቸውን እየቀሙ እያሰሩዋቸው ነው።
በሌላ በኩል ትናንት ምሽት በጎንደር ከተማ ተጨማሪ የቦንብ ጥቃት የተፈጸመ ሲሆን፣ አንድ ታጣቂ ግለሰብ ጥቃቱን ባደረሱት ሃይሎች ተመትቶ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ ጥቃቱ በቀጠናው የህወሃት ወኪል በመሆን የደህንነት ስራ ይሰራል በተባለው በአቶ አማረ አምባየ ላይ ያነጣጠረ እንደነበር ለኢሳት የደረሰው መረጃ ያሳያል። ግለሰቡ እና ጠባቂው ጉዳት ደርሶባቸው ለህክምና ወደ አዲስ አበባ መላካቸውንም መረጃው አክሎ አመልክቷል።
ጥቃቱን ተከትሎ ከሙሴ ባምብ ወታደራዊ ካምፕ የተንቀሳቀሰ አንድ ኦራል መኪና ከምሽት 5 ሰአት አካባቢ ልዩ ስሙ የኢትዮጵያ ካርታ በሚባለው ስፍራ ላይ በጥይት ተመትቶ ሲገለበጥ 4 ወታደሮች ወዲያውኑ ህይወታቸው ሲያልፍ፣ 5 ወታደሮች ደግሞ ቆስለዋል። መኪናው ዛሬ ተጎትቶ ጎንደር አዘዞ ወደሚገኘው ወታደራዊ ካምፕ ተወስዷል። የቆሰሉ ወታደሮችም አዘዞ በሚገኘው የጦር ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ሲሆን፣ ሟች ወታደሮችም አዘዞ ሎዛ ማሪያም ቤ/ክርስቲን ተቀብረዋል፡፡
የአሁኑ ጥቃት በአንድ ሳምንት ጉዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ መፈጸሙ ነው። በሰራባ የመስኖ ፕሮጀክት አካባቢ ተደጋጋሚ ጥቃቶች የተፈጸሙ ሲሆን፣ ጥቃቱን በሚያደርሱ ታጋዮች ላይ እስካሁንም ምንም ጉዳት አልደረሰባቸውም።
ገዢው ፓርቲ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አማካኝነት ማንኛውንም አይነት የተቃውሞ እንቅስቃሴ ተቆጣጥሬዋለሁ ቢልም፣ አሁንም በሰሜን ጎንደር የተለያዩ ወረዳዎች ጥቃቶች እየተፈጸሙ ነው።