በሰሜን ጎንደር የሚንቀሳቀሱ የነጻነት ሃይሎችን ለማጥቃት አዲስ እንቅስቃሴ ተጀመረ

ታኅሣሥ  ፭ (አምስት)ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :-የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት በቅርቡ በዞኑ የተለያዩ ግንባሮች በተደረጉ ውጊያዎች ከፍተኛ ሽንፈት የደረሰበት የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ፣ ዛሬ ረዕቡ ማለዳ ጀምሮ በርካታ ወታደሮችን የጫኑ ተሽከርካሪዎችን ወደ ወልቃይት አሰማርቷል። አዲሱ እንቅስቃሴ የጸረ ሽምቅ አዛዥ ኮማንደር ዋኘው አዘዘ መታሰራቸውን ተከትሎ የታቀደ ሲሆን፣ ቀደም ብለው የተደረጉት ተመሳሳይ ዘመቻዎች ሳይሳኩ ቀርተው ነበር። ለውጤት መጥፋቱ ተጠያቄ የተደረጉት ኮማንደር ዋኘው ሲሆኑ፣ የአሁኑን ዘመቻ ደግሞ የህወሃት ታማኝ መኮንኖች ይመሩታል ተብሎአል።

ሰፋ ያለ ወታደራዊ ጥቃት ለመሰንዘር ያቀደው ገዢው ፓርቲ፣ ጥቃቱን ማክሸፍ ከተቻለ በአገዛዙ ላይ ከፍተኛ የስነ ልቦና ኪሳራ እንደሚደርስበት ምንጮች ገልጸዋል። “ሁለት ጊዜ ተመሳሳይ እንቅስቃሴዎች ተደርገው ከሽፈዋል፣ ይህም ይከሽፋል” በማለት ያነጋገርናቸው ታጋዮች ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በጎንደር በአዘዞ ማክሰኝት እና ጸዳ የአርበኞች የጎንደር ወጣቶች ክንፍ ወረቀት በትኗል። በተበተነው ወረቀት ላይ ወጣቶን እየጠቆሙ የሚያሳስሩ ሰዎች ከዚህ ድርጊታቸው እንድቆጠቡ ያሳስባል።