በምስራቅ ሀረርጌ ዞን የሚገኙ የሀገር ሽማግሌዎች ለአቤቱታ አዲስ አበባ ገቡ

(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 18/2009) በምስራቅ ሀረርጌ ዞን የሚገኙ የሀገር ሽማግሌዎች በልዩ ፖሊስ የሚፈጸመውን ጭፍጨፋ በመቃወም ለአቤቱታ አዲስ አበባ መግባታቸው ተነገረ።

የሀገር ሽማግሌዎቹ በልዩ ፖሊስ በሕዝብ ላይ የሚደርሰው ስቃይ እንዲቆም አቤቱታቸውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቅርበዋል።
ከምስራቅ ሀረርጌ ወደ አዲስ አበባ ለአቤቱታ የመጡት የሀገር ሽማግሌዎች ባለፉት ወራት ብቻ በልዩ ፖሊስ የተገደሉት ሰላማዊ ሰዎች ቁጥር 55 መድረሱን ተናግረዋል።

በሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊስ በሚል በ1999 የተቋቋመው ታጣቂ ሐይል ነዳጅ በማውጣት ላይ በነበረው የቻይና ኩባንያ የተቀጠሩ 74 ኢትዮጵያውያን 9 ቻይናዊያን በጅምላ ከተገደሉ በኋላ ነበር።

ጅምላ ግድያውን የኦጋዴን ነፃ አውጭ ግንባር ፈፅሞታል በሚል ከዚህ ቡድን ጋር ይፋለማሉ ተብለው የተቋቋሙት የልዩ ፖሊስ አባላት ግን ፊታቸውን ወደ ሰላማዊ ሰዎች በማዞር ከፍተኛ ጭፍጨፋ እያካሄዱ መሆናቸውን የምስራቅ ሐረርጌ የሀገር ሽማግሌዎች ይገልፃሉ።

ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሐረርጌ ጉርሱም ወረዳ የመጡት የሀገር ሽማግሌዎች በአካባቢው ያለው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን በአቤቱታቸው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አሳውቀዋል።

አቶ ኡስማን ኦማር የተባሉት የሀገር ሽማግሌዎች ተወካይ አዲስ ስታንዳርድ ለተባለው የዜና አውታር እንደገለፁት የሶማሌ ልዩ ፖሊስ አባላት ከግድያ በተጨማሪ ዘረፋ፣ አስገድዶ መድፈርና ሌሎችንም የሰብዓዊ ሰቆቃዎችን እየፈፀሙ ይገኛሉ።

እነዚሁ ሰቆቃ የተፈፀመባቸው 8 የኦሮሚያ አካባቢዎች በቀቃ፣ ቆሬ፣ ወራ ጉዬ፣ ወረኢሉ፣ ኩልማያ፣ ኖሊየ እና ባኮ የተባሉ መንደሮች መሆናቸውን የሀገር ሽማግሌዎቹ ገልፀዋል።

ይህ ሁሉ ግድያና ሰቆቃ ሲፈፀምም የኦሮሚያ ክልል ሕይወታችንን ሊታደግ አልቻለም ብለዋል።
ባለፉት 8 ወራት ብቻ 55 ሰላማዊ ወገኖቻችን ተገድለዋል ሲሉም በምሬት ተናግረዋ።

እራሳቸውን እንዳይከላከሉ እንኳ የእጅ የጦር መሣሪያቸውን እንደተነጠቁም በአቤቱታቸው ገልፀዋል።

የኦሮሚያ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ አዲሱ አረጋ የሶማሌ ልዩ ፖሊስ የግዛት ይገባናል በሚል በምስራቅ ሐረርጌ ግድያ እንደሚፈፀም ገልፀዋል።

የልዩ ፖሊስ ሀይሉ የሶማሌ የክልል አርማና ባንዴራ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች እየተከለ መሆኑንም ነው ያስታወቁት።

በምስራቅ ሐረርጌ የሀገር ሽማግሌዎች አቤቱታ የቀረበለት የፌዴሬሽን ምክር ቤት እስካሁን ለጥያቄው ምላሽ አልሰጠም።