በሜዲትራኒያን ሁለት ጀልባዎች መስመጣቸውን ተከትሎ ከ200 በላይ መንገደኞች ሞተው ሊሆን ይችላል ተባለ

ኢሳት (መጋቢት 15 ፥ 2009)

ከሊቢያ ወደ ጣሊያን በማቅናት ላይ የነበሩ ሁለት ጀልባዎች በሜዲትራኒያን ባህር ላይ የመስጠም አደጋ አጋጥሟቸው ከ200 በላይ መንገደኞች ሞተዋል የሚል ስጋት ማሳደሩን የነብስ አድን ሰራተኞች አስታወቁ።

እያንዳንዳቸው ከ100 በላይ ስደተኞችን አሳፍረው ይጓዙ የነበሩት ጀልባዎች ከአቅማቸው በላይ ሰው በመጫናቸው ምክንያት አደጋው ሊደርስ መቻሉን የስፔን የግረሰናይ ድርጅትን ዋቢ በማድረግ ሮይተርስ ዘግቧል።

ፕሮአክቲቭ ኦፐን አርምስ (Proactive Open Arms) የተሰኘው ይኸው ተቋም የሰው ህይወት ለማትረፍ በተካሄደው ርብርብ አምስት አስከሬን ብቻ በፍለጋ መገኘቱን ገልጿል።

በነብስ አድን ስራው በህይወት የተገኘ ሰው ባለመኖሩም ወደ 240 የሚጠጉ ተጓዦች ሊሞቱ ይችላሉ የሚል ስጋት ማሳደሩን የግብረሰናይ ድርጅቱ ተወካይ ላውራ ላኑዛ አስረድተዋል። የጣሊያን የባህር ሃይል አካላት በበኩላቸው ሃሙስ ከደረሰው አደጋ የሰው ህይወትን ለማትረፍ በተካሄደ ዘመቻ የአምስት ሰዎች አስከሬን መገኘቱን አረግጠዋል።

ይሁንና የጣሊያን የባህር ሃይል አካላት በጀልባዎቹ ምን ያህል ሰው ተሳፍሮ እንደነበር አለመታወቁንና የድረሱልን ጥሪ እንዳልደረሳቸው ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ሁለቱ ጀልባዎች የተለያዩ ሃገራት ስደተኞችን በመያዝ ወደጣሊያን በማቅናት ላይ የነበሩ ሲሆን ባለፉት ሶስት ወራቶች ብቻ ከ20ሺ የሚበልጡ ስደተኞች ከሊቢያ ወደ ጣሊያን መግባታቸውን የአለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት (IOM) መረጃ የመለክታል። በዚሁ አስቸጋሪ ጉዞ በተመሳሳይ ጊዜ ወደጣሊያን ለመግባት ሙከራን ካደረጉ መካከል ወደ 599 ስደተኞች መሞታቸውንም ተገልጿል።

ከሊቢያ መውጫን አጥተው የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት ዜጎች በሃገሪቱ ከሚደርስባቸው እንግልትና ሰቆቃ ለማምለጥ ሲሉ ህይወታቸውን ለአደጋ በሚያጋልጥ ሁኔታ ወደ ጣሊያን/አውሮፓ በማቅናት ላይ እንደሆኑ የስደተኛ ድርጅቶች ይገልጻሉ።

የአውሮፓ የክረምት ወቅት በመገባደድ ላይ መሆኑን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ከሊቢያ ወደ አውሮፓ በተለይ ወደጣሊያን ለመጓዝ በዝግጅት ላይ እንደሆኑም ተመልክቷል።

“የሚያዚያ ወር ከመግባቱ በፊት ታይቶ የማይታወቅ የስደተኛ ቁጥር ወደ አውሮፓ ለመግባት ዋጋን እየከፈለ ይገኛል” ሲሉ የስደተኛ ድርጅቱ (IOM) ቃል አቀባይ ዶ’ኦል ሚልማን ለቢቢሲ አስረድተዋል።

በተያዘው ወር ከሊቢያ ወደ አውሮፓ ለመግባት የተደረጉ የስደተኞች ሙከራ ከመቼውም ጊዜ በላይ በመጠን ልቆ መገኘቱን እና ቁጥሩ በበጋው ወቅት ሪከርድን ሊያስመዘግብ እንደሚችል ሚልማን አክለው ገልጸዋል። በሁለቱ ጀልባዎች ሲጓዙ የነበሩ ስደተኞች ማንነት እስካሁን ድረስ አለመታወቁን ለመረዳት ተችሏል።