በሚቀጥሉት ሁለት ወራት 2 ሚሊዮን ኢትዮጵያ በጎርፍ አደጋ ተጋላጭ እንደሚሆኑ ተነገረ

ኢሳት (ነሃሴ 18 ፥ 2008)

በቀጣዮቹ ሁለት ወራቶች ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በጎርፍ አደጋ ተጋላጭ እንደሚሆኑ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ረቡዕ አሳሰበ

በሃገሪቱ በተከሰተው የድርቅ አደጋ ዙሪያ ሪፖርቱን ያወጣው ድርጅቱ ከሚያዚያ ወር ጀምሮ 600 ሺ ሰዎች በጎርፍ አደጋ ከቀያቸው ሊፈናቀሉ መቻላቸውን እንደገለጸ ሮይተርስ የተባበሩት መንግስታት መንግስታት ድርጅትን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።

በጎርፍ አደጋ ጉዳት የሚደርስባቸው ሰዎች በሃገሪቱ ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ የተጋለጡ ሰዎች ቁጥር እንዲጨምር ያደርጋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ 20 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ግዛት በዚሁ የጎርፍ አደጋ ጉዳት ይደርስበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሶማሊ፣ አፋር፣ ሃረሪ እና የደቡብ ክልሎች የጎርፍ አደጋው ከፍተኛ ጉዳት ያደርስባቸዋል ተብለው ከሚጠበቁት ክልሎች ዋነኞቹ መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።

በአሁኑ ወቅት ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ የተጋለጡ ሰዎች ቁጥር ወደ 10 ሚሊዮን አካባቢ ሲሆን፣ የጎርፍ አደጋው ቁጥሩን ከፍ እንዲል በማድረግ የእርዳታ አቅርቦቱ ላይ ጫናን ያሳድራል ተብሎ ተሰግቷል።

ካለፈው አመት ጀምሮ ከ40 የሚበልጡ ሃገራትና የእርዳታ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ለተከሰተው የድርቅ አደጋ ከ700 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍን ያደረጉ ሲሆን፣ አሁንም ድረስ ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ ለመረዳት ተችሏል።

በጅቡቲ ወደብ ተፈጥሮ ያለው የዕቃዎች መጨናነቅ የእርዳታ አቅርቦቱ ለተረጂዎች እንዳይደርስ እንቅፋት መፍጠሩንና በአሁኑ ወቅት ከ10 በላይ መርከቦች የእርዳታ እህልን እንደጫኑ በወደቡ ወረፋን እየተጠባበቁ እንደሚገኝ የወደቡ ባለስልጣናት ይገልጻሉ።

ከግማሽ ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ የእርዳታ እህልን የጫኑት መርከቦት ካለፈው ወር አጋማሽ ጀምሮ የጫኑትን የእርዳታ እህል ማራገፍ እንዳልቻሉ ለመረዳት ተችሏል።