በመጪው የእሬቻ በአል ያለፈው አመት ግድያና እልቂት እንዳይደገም ሂዩማን ራይትስዎች አሳሰበ

(ኢሳት ዜና–መስከረም 9/2010) በመጪው የእሬቻ በአል ያለፈው አመት ግድያና እልቂት እንዳይደገም የኢትዮጵያው አገዛዝ ታጣቂዎች ከሀይል ርምጃ እንዲቆጠቡ ሂውማን ራይትስ ዎች አሳሰበ።

የኦሮሞ የእሬቻ በአል ላይ ባለፈው አመት የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ጣልቃ በመግባት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተተኮሰባቸው ጥይትና ይህንን ተከትሎም በደረሰው መተፋፈግ መገደላቸውን አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ተቋም አስታውሷል።

በዘንድሮው በአልም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በሚገኙበት በዚህ በአል ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይፈጸም የአገዛዙ ታጣቂዎች ከሀይል እርምጃ እንዲቆጠቡ አሳስቧል።

የእሬቻ በአል ዝናቡ አብቅቶ የሰብል መሰብሰቢያ ወቅት መምጣቱን በምስጋና ለማሰብ በታላቅ ድምቀት የሚከበር የኦሮሞ ባህል ነው።

በአሉ የሰላምና የደስታ መግለጫ ቢሆንም በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ በጸጥታ ጥበቃ ስም የታጠቁ ወታደሮችንና የፖለቲካው አራማጅ የሆኑ አባገዳዎችን በማሰማራት ባለፈው አመት የነበረውን ስነስርዓት መበጥበጡን የሚያሳይ መረጃ እንዳለው ሂዩማን ራይትስዎች ገልጿል።

ባለፈው አመት በኦሮሚያ የነበረውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ስጋት የገባው በህወሃት የሚመራው አገዛዝ አካባቢውን የጦር ቀጠና አድርጎት እንደነበር ይታወሳል።
የተኩስ ሩምታው በሔሊኮፕተር ታግዞ የተጀመረው ደግሞ የሕወሃት አገዛዝ ይብቃ የሚል መፈክር በአንድ ወጣት መስተጋባቱን ተከትሎ ነው።

ሒዩማን ራይትስዎች እንዳስታወሰው የአገዛዙ ታጣቂዎች ሕዝብ ላይ በመተኮሳቸውና መግደል በመጀመራቸው መጨናነቅና መተፋፈግ ተፈጥሮ በርካታ የሀገሪቱ ዜጎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

እናም ይህ ጅምላ ጥቃት ዘንድሮም እንዳይደገም አገዛዙ ከወዲሁ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ ሂውማን ራይትስዎች አሳስቧል።
እንደ ሰብአዊ መብት ተከራካሪው ገለጻ ሕዝቡ አሁንም በአገዛዙ ላይ ከፍተኛ ጥላቻና ተቃውሞ ስላለው በአጋጣሚው ድምጹን ሊያሰማ ይችላል።

በዚሁ በአል የሞቱትን ሰማዕታትም ሊያስባቸው የግድ ነው ብሏል።በመሆኑም በቢሾፍቱ ሆራ ሃይቅ በሚከበረው የእሬቻ በአል ያለፈው አይነት ግድያ እንዳይፈጸም ሒዩማን ራይትስዎች ስጋቱን ገልጿል።

ባለፈው አመት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በእሬቻ በአል ላይ የመገደላቸው ጉዳይ በገለልተኛ አካል እንዳይጣራ በመደረጉ ተጠያቂ አካል እንዳይኖር አድርጓል ሲል ተቋሙ አስታውሷል።

አገዛዙ በራሱ መርማሪዎች ጉዳዩን አጣራለሁ ቢልም ገለልተኛ አካል ግድያውን እንዳያጣራ ከልክሎ እንደሚገኝ ሒዩማን ራይትስዎች ገልጿል።