በመላ ሃገሪቱ በሚታየው የነዳጅ እጥረት ተጓዦች ከታሪፍ በላይ በመክፈል መቸገራቸውን ተናገሩ፡፡

የካቲት ፫ ( ሦስት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በበርካታ የሃገሪቱ ከተሞች የሚታየው የነዳጅ እጥረት ተባብሶ በመቀጠሉ ምክንያት ተጓዦች ከመደበኛ ታሪፍ በላይ እንዲከፍሉ እየተገደዱ መሆኑን ለኢሳት ገለጹ፡፡
በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ከወራት በፊት የተከሰተው የነዳጅ እጥረት ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ በተለይ በአማራ ክልሏ በበርካታ ከተሞች የቤንዚን አገልግሎት ከተቋረጠ ሳምንታት መቆጠሩን አሽከርካሪዎች ተናግረዋል።
በባህር ዳር፣ጎንደር ፣ወልዲያና ደሴ በመሳሰሉት ትልልቅ ከተሞች የነዳጅ አገልግሎት ባለመኖሩ በጀሪካን በመቅዳት ለመገለልገል መገደዳቸውን የሚናገሩት አሽከርካሪዎች፣ በተከታታይ ለሁለት ወራት በነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ ቢደረግም አገዛዙ በሁሉም ከተሞች የትራንስፖርት አገልግሎት የዋጋ ማስተካከያ ባለማድረጉ መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡
አሽከርካሪዎች ለዘጋቢያችን አክለው እንደተናገሩት ከገዥው መንግስት አመራሮች ጋር የጥቅም ግንኙነት ያላቸው የማደያ ባለ ሃብቶች ቀደም ብለው ያከማቹትን ነዳጅ በድብቅ በመቅዳት በጀሪካን በከፍተኛ ዋጋ በመሸጣቸው በትራንስፖርት ዋጋ ላይ እስከ ሃምሳ በመቶ ድረስ ጭማሪ በማድረግ ለመስራት ተገደዋል።
በነዳጅ ላይ የዋጋ ጭማሪ ማውጣቱን ተከትሎ የገዥው መንግስት በትራንስፖርት ዋጋ ላይ የሚደረገውን ማስተካካያ ፈጥኖ ባለማድረጉ የትራንስፖርት የዋጋ ተመን የሚወስኑት የመነኸሪያ ደላሎች መሆናቸውን የሚናገሩት ተጓዦች፣ በየመነኻሪያው የሚሰሩ የትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎችም ጉዳዩን እንዳላዩ ሆነው ማለፋቸው እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል፡፡
የገዥው መንግስት “የጥልቅ ተሃድሶ በማካሄድ የተሻለ ለመስራት እየተንቀሳቀስኩ ነው” ቢልም በተለያዩ መስሪያ ቤቶች በተጨባጭ የሚታየው ግን ከበፊቱ ያልተለወጠ አሰራር መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ።