በመላ ሀገሪቱ እየቀጠለ ባለው ተቃውሞና እየተወሰደ ባለው የኅይል እርምጃ ዙሪያ የተጠናከረ ሪፖርታዥ

ነሃሴ  ( ሃያ ሰባ ) ቀን ፳፻፰ / ኢሳት ዜና :- በደቡብ ጎንደር ዞን በደራ ወረዳ በአርብ ገበያ በአርሶ አደሮችና በመከላከያ አባላት መካከል የተኩስ ልውውጥ እየተካሄደ ነው።

የግጭቱ ምክንያት ትናንት ምሽት ከእስቴይ ወረዳ 90 ኩንታል ጤፍ ጭኖ የመጣ የጭነት መኪና አርብ ገበያ ሲደርስ በህዝብ እንዲቆም ከተደረገ በኋላ ወደ መጣበት እንዲመለስ በመደረጉ ነው

« ህዝቡ ከእንግዲህ ጤፍም ሆነ ሌላ ማናቸውም እህል ከአካባቢያችን ወደሌላ ሥፍራ አይንቀሳቀስም በሚል ተቃውሞ መኪናውን ማስቆሙን የገለጹት የዓይን ምስክሮች፣ ከጥቂት ሰዓታት እገታ በኋላ ወደመጣበት ወደ እስቴ ወረዳ እንዲመለስ መደረጉን ተናግረዋል።

ይህን ተከትሎ ዛሬ ማርፈጃውን በአርሶ አደሮችና በመከላከያ አባላት መካከል የተኩስ ልውውጥ ሲደረግ መዋሉን ከስፍራው የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። ሰሞኑን በደራ ወረዳ ደማቅ ሰላማዊ ሰልፎች ሲደረጉ መሰንበታቸው ይታወቃል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ትናንት በአምባ ጊዮርጊስ በተደረገው ግጭት 18 የመከላከያ አባላትና ከአርሶ ደሮች በኩል 30 የሚሆኑ መገዳላቸውን ተከትሎ በዛሬው ዕለት የአጋዚ ታጣቂዎች በከተማው ቤት ለቤት እየዞሩ ሳይቀር በበርካታ ወጣቶች ላይ መጠነ ሰፊና ዘግናኝ እርምጃ እየወሰዱ ይገኛሉ።

ከእርምጃው የተረፉ በርካታየከተማዋ ወጣቶች ጫካ መመሸጋቸውም ታውቋል” እንደ ዓይን እማኞቹ ገለጻ ግጭቱ የተካሄደው በአምባ ጊዮርጊስ ህዝቡ እያደረገ ያለውብ ትግል ለማገዝ ከሁለት የገጠር ቀበሌዎች በመጡ አርሶ አደሮችና በአጋዚ አባላት መካከል ነው።

በግጭቱ ከመከላከያ ወገን 18 ሲሞቱ ሰላማዊ ዜጎችን ጨምሮ ከአርሶ አደሮቹ በኩል 30 መሰዋታቸውን የገለጹት የዓይን ምስክሮቹ፤ ሁሉም መስዋዕት የሆኑት አርሶ አደሮች ባዶ እጃቸውን ተሰልፈው የመጡ መሆናቸውንና ከታጠቁት አርሶ አደሮች ግን አንድም ሰው አለመሞቱን ተናግረዋል ።

ይህን ተከትሎ ወደ 400 የሚጠጉ ሰዎች ከመታሰራቸውም በላይ ዛሬ በከተማው ወጣቶች ላይ የኃይል እርምጃ እየተወሰደ መሆኑንና በከተማዋ በአብዛኛው ሴቶች ብቻ መቅረታቸውን የጠቀሱት የዓይን ምስክሮቹ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎናቸው በመቆም እንዲያግዛቸው ጥሪ አቅርበዋል።

በተመሳሳይ የታጠቁ ሓይላት በወሰዱት መጠን ያለፈ አርምጃ ህጻናት ተጎጅዎችን ጨምሮ የጎንደር ሆስፒታል በቁስለኞች መጨናነቁን የኢሳት ወኪሎች ከስፍራው ገልጸዋል።  ክፉኛ ተመትተው በሆስፒታሉ ህክምና አየተደረገላቸው ካሉት መካል ከኣስር ዓመት በታች የሆኑ ዘጠን ህጻናት አንደሚገኙበት ምንጮቹ ገልጸዋል።

በውጪ በሚንቀሳቀስ ማናቸውም ሰው ላይ አየተኮሱ አርምጃ የሚወስዱት ወታደሮች ከሱዳን የመጡ መሆናቸውን ኣረጋግጠናል የሚሉት ምንጮቹ የሚነጋገሩትም በአንግሊዝኛ ቁዋንቁዋ ነው ብለዋል።

ለጥቃት ያጋለጠን ከቢት ያለመውጣት ተቃውሞው ነው የሚሉት የኣካባቢው ወጣቶች፣ ከአንግዲህ ሊላ መንገድ ለመከተል ውሳነ ላይ ደርሰናል ብለዋል።

ከ አንግዲህ  ኣይናችን አያዪ አንዲሁ ኣንሞትም ያሉት ወጣቶቹ፣ << አየገደልን አንሞታለን፣ ቢጨርሱንም አኛ ሞተን ለመጪው ትውልድ ነጻነት አናወርሳለን>> ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በደርብረታቦርና ጋይንት አካባቢ አሁንም ግድያው ተጠናክሮ ቀጥሏል። ወጣቶች ወደ ጫካ በመግባት ትግሉን ተቀላቅለዋል። በደብረታቦር እስርቤትም የተቃጠለው ሆን ተብሎ በአጋዚ ታጣቂዎች መሆኑ ተረጋግጧል። የዓይን እማኞች እንዳሉት ከአስር በላይ ወጣቶች በማረሚያ ቤቱ ውስጥ እንዳሉ በእሳት እና በጥይት ተገለዋል። የሟቾቹን አስከሬን ቤተሰቦቻቸው ከሆስፒታል ወስደው ለመቅበር ተከልክለዋል።በሌላ በኩል በከፍተኛ ደረጃ የታጠቁ ወታደሮችን የጫኑ በበርካታ አውቶቡሶች፣ ፓትሮሎች፣ ኦራል መኪናዎችና ሌሎች ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ወደተለያዩ የጎጃምና የጎንደር ከተሞች ሲጓጉዙ ውለዋል።

ማለዳ ላይ ከፊትና ከኋላ በፓትሮል የታጀቡና በአራት አውቶቡስ የተጫኑ የመከላከያ አባላት ከደብረማርቆስ ተነስተው ወደ ማንኩሳና ባህርዳ ስለተንቀሳቀሱ ህዝቡ ከወዲሁ የጥንቃቄ እርምጃዎችን እንዲወስድ ጥሪ ቀርቧል።

በተመሣሳይ በአሁኑ ሰዓት የታጠቁ ወታደሮችን የጫኑ በርካታ የኦራል መኪኖች ከመርዓዊ ወደ ባህርዳርና ጎንደር በመንቀሳቀሳቸው ህዝቡ የጥንቃቄ እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ ተላልፏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ  በደቡብ ወሎ የኮምቦልቻ ወጣቶች ከነሀሴ 30 ቀን ጀምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ከቤት ውስጥ ያለመውጣት አድማ ጥሪ አደረጉ።

የወጣቶቹ አስተባባሪዎች ከትናንት ምሽት ጀምሮ በከተማው ባሰራጩት የጥሪ ወረቀት ማናቸውም የመንግስትና የግል ተቋማት ሰራተኞች እና ነጋዴዎች በተጠቀሱት ቀናት ምንም አይነት ሥራ ባለመስራትና ከቤት ባለመውጣት በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች በገፍ እየተገደሉ ላሉ ወገኖቻቸው አጋርነታቸውን እንዲገልጹ ጥሪ አቅርበዋል ።

« ህዝባዊ ተቃውሞው እንዳስፈላጊነቱን አድማሱንና ስልቱን እየቀየረ ሊቀጥል እንደሚችል ያስታወቁት አስተባባሪዎቹምም ትግሉን ከዳር የሚያደርሱ ወጣቶች በአመራርነት መመረጣቸውን አስታውቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአማራና ኦሮሚያ ህዝብ ላይ የሚያደርሰውን የዘር ማጥፋት ዘመቻ ለአለም ህዝብ ለማሳወቅ ነገ ቅዳሜ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 3፡00 ሰዓት እስከ 4:00 ስዐት ድረስ የትዊተር ዘመቻ ይካሄዳል።

የትዊተር አካውንት ያላቸው በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በዘመቻው ተሳትፎ በማድረግ በወገኖቻቸው ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግፍ ለዓለማቀፉ ማህበረሰብ እንዲያሳውቁና የትዊተር አካውንት የሌላቸው ደግሞ በቶሎ እንዲከፍቱና ማስረጃዎችን አሰባስበው እንዲጠብቁ አስተባባሪዎቹ ጥሪ አቅርበዋል።

እንዲሁም በአዲስ አበባ የፊታችን እሁድ ከቤት ያለመውጣት አድማ ጥሪ የተደረገ ሲሆን፣ በከተማዋ ብዛት ያላቸው የመከላከያ ኣባላት መሰማራታቸውና  በየመንገዱ ሰዎችን  መፈተሽ ጀምረዋል።

መንግስት መጠነ ሰፊ የሃይል አርምጃ አየወሰደ ቢገኝም ህዝባዊ ተቃውሞው ስልቱን አየቀየረና ኣድማሱን አያሰፋ በመላ ሀገሪቱ በመቀጣጠል ላይ ነው። በኦሮሚያ ክልልና በኣገር ኣቀፍ ደረጃ ኣጠቃላይ የግዥና ሽያጭ ኢኮኖሚያዊ ተቃውሞ ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል።