በለገጣፎ ለገዳዲ አካባቢ ለእስር ተዳርገው የነበሩ ወጣቶች ፣ ችግሩ እስካልተፈታ ድረስ ትግላቸውን እንደሚቀጥሉ አስታወቁ

መስከረም ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በኦሮሚያ ልዩ ዞን በለገጣፎ ለገዳዲ አካባቢ ከመሬት ጋር በተያያዘ የሚፈጸመውን ሙስና በመቃወማቸው ለእስር ተዳርገው የነበሩ 7 ወጣቶች ባለፈው ቅዳሜ ህዝቡ ባሳየው ተቃውሞ በ21 ሺ ብር የዋስትና ገንዘብ እንዲፈቱ መደረጉ ታውቋል። ወጣቶቹ በዛሬው እለት ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ቀጠሮ ተሰጥቷቸው የነበረ ቢሆን፣ አቃቢ ህግ ስትጠሩ ትመጣላችሁ በማለት አሰናብቷቸዋል።

ታስረው ከተፈቱት ወጣቶች መካከል መኮንን ተስፋየ “አቃቢ ህግ መንግስት ሞቷል፣ መንግስት የለም ብለህ ቀስቅሰሀል ” ተብሎ እንደተከሰሰ ገልጧል። ወጣቱ እንደሚለው ቀስቅሰሃል ተብሎ በተከሰሰበት ቀን ለስራ ውድድር አዲስ አበባ እንደነበር ገልጧል

በአካባቢው በሚኖሩ አርሶአደሮችና እና ባልተማሩ ሰዎች ይዞታ ላይ የመንግስት ባለስልጣናት ስለሚፈጽሙት ሙስና የመንግስት ኮሚኒኬሽን ሰራተኛ የሆነው ወጣት መኮንን በዝርዝር ያስረዳል

የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት በአካባቢው የሚታየውን ህገወጥ የመሬት ዝርፊያ ለመቆጣጠር ቃል ገብተው ቢሄዱም አንዱም ሊያስተካክሉት እንዳልቻሉ ወጣት መኮንን ገልጧል

በለገጣፎ ለገዳዲ አካባቢ በአንድ የመኖሪያ ቦታ ላይ ከአንድ በላይ የሆኑ ሰዎች የባለቤትነት ካርታ እንደሚይዙ ወጣት መኮንን ተናግሯል የወረዳው የምክር ቤት አባል እና የቋሚ ኮሚቴ አባል የሆነው አቶ ሲሳይ ለማ ጉርሙ በበኩሉ ከቀበሌ እስከ ከንቲባ ያሉ የሃላፊነት ቦታዎች በሙሉ በዘመድ እና በወዳጅነት የተያዙ በመሆናቸው ሙስናን ለመዋጋት አልተቻለም

በለገጣፎ ለገዳዲ አካባቢዎች ከመሬት ጋር በተያያዘ በሚፈጸመው ሙስና የመንግስት ባለስልጣናት የፌደራሉና የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት እጃቸው እንዳለበት የአካባቢው ነዋሪዎች ሲገልጹ ይሰማል።