ስዊድናውያንኑ ጋዜጠኞች ላይ መንግስት የያዘው የተለየ አቋም የለም ሲሉ አቶ በረከት ስምዖን ተናገሩ

የካቲት 5 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶባቸው የ 11 ዓመት እስራት በተበየነባቸው ስዊድናውያን ጋዜጠኞች ላይ መንግስት የያዘው የተለየ አቋም የለም ሲሉ አቶ በረከት ስምዖን ተናገሩ።

የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስትርና የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ በረከት ስምዖን ጋዜጠኞቹ ይቅርታም ቢጠይቁ በቅርቡ ሊፈቱ እንደማይችሉ የጠቆሙት፤አቶ መለስ ፓርላማ ቀርበው ጋዜጠኞቹ ይቅርታ ከጠየቁ ሊፈቱ እንደሚችሉ ፍንጭ መስጠታቸው በዓለማቀፍ ብዙሀን መገናኛዎች ይፋ በሆነ ማግስት ነው።

አቶ በረከት በጉዳዩ ዙሪያ  በቃለ-ምልልስ መልክ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል በሰጡት መግለጫ፤ ስዊድናውያኑ ጋዜጠኞች ይፈቱ ዘንድ በመንግስት ላይ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ጫና ሲደረጉ መቆየታቸውን በመጥቀስ፤ከነዚህም ግፊቶች ውስጥ አንዱ ጋዜጠኞቹ በይቅርታ እንዲፈቱ የሚደረግ ግፊት እንደሆነ ተናግረዋል።

በመንግስት በኩል ያለው ሀሳብ በመጀመሪያ ሰዎቹ ጥፋት ፈፅመው በመገኘታቸውና በህጋዊ ፍርድ ቤት የተቀጡ በመሆናቸው ፍርድ ቤቱ የወሰነባቸውን ቅጣት ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው የሚል ነው ያሉት አቶ በረከት፤ “ይህ ከሆነ በሁዋላ ነው ስለሌላ ነገር ማሰብ የሚቻለው”ብለዋል።

አቶ በረከት አያይዘውም፦“ጋዜጠኞቹ በአሁኑ ጊዜ ጥፋተኝነታቸውን ተከትሎ የተበየነባቸውን ቅጣት ገና “ሀ” ብለው እየጀመሩ ባሉበት ሁኔታ መንግስት ስለሌላ ነገር የሚያስብበት ምንም ዓይነት ሁኔታ የለም” በማለት ጋዜጠኞቹ ይቅርታ ቢጠይቁም በቅርቡ ሊፈቱ እንደማይችሉ ጠቁመዋል።

“ሰዎቹ ቅጣታቸውን ተግባራዊ በሚያደርጉበት ጊዜ በማረሚያ ቤት ቆይታቸው የሚኖራቸው ፀባይና ሥነ-ምግባር በሂደት የሚታይበት ሁኔታ ይኖራል”ያሉት አቶ በረከት፤”ማናቸውንም ውሳኔ ለማሳለፍ ፤እነዚህ  ነገሮች ሁሉ መሟላት አለባቸው፤ከውጪ የሚመጣ ማናቸውም ጫና ውጤት ይኖረዋል የሚል ግምት የለኝም”ብለዋል።

አቶ መለስ ጋዜጠኞቹ ይቅርታ ከጠየቁ ሊፈቱ እንደሚችሉ ፍንጭ በሰጡ ማግስት አቶ በረከት ጋዜጠኞቹ ይቅርታ ቢጠይቁም በቅርቡ ሊፈቱ እንደማይችሉ መናገራቸው ብዙዎችን አስገርሟል።

ጋዜጠኛ ምርቲን ሽብዬ እና ጆሀን ፐርሰን ፤በ ፍረድ ቤቱ ሂደት ተስፋ በመቁረጣቸው በኢትዮጵያ የሽምግልና ባህል መሰረት በይቅርታ ለመፈታት እንደሚፈልጉ መግለፃቸው ይታወሳል።

ሁለቱን ስዊድናውያን ጋዜጠኞች ጨምሮ የ ኢትዮጵያ መንግስት የሽብርተኝነት ክስ መስርቶ ያሰራቸውን ጋዜጠኞችና የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች እንዲፈታ፤ ዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማትና የፕሬስ ነፃነት ተሟጋቾች በተደጋጋሚ እያሣሰቡ ይገኛሉ።