ሳውዲአረቢያ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ከሀገሯ በሃይል እንዳታባርር ሒዩማን ራይትስ ዎች ተማጸነ

(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 19/2009) ከግማሽ ሚሊየን የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ከሀገሯ በሃይል እንዳታባርር ሒዩማን ራይትስ ዎች ሳውዲአረቢያን ተማጸነ።

የሳውዲአረቢያ መንግስት በሀገሪቱ የሚገኙና የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያንን በሃይል እንደሚያስወጣ ትላንት ሀሙስ አስታውቋል።

በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ከሳውዲአረቢያ እንዲወጡ ግፊት ቢያደርግም በተቀመጠው ጊዜ ገደብ ውስጥ የወጡት 45 ሺህ ብቻ ናቸው።

ሌሎች ከ5 መቶ ሺ በላይ የሚሆኑት በሳውዲአረቢያ የሚኖሩና ህጋዊ ፈቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ግን በሀገራቸው ያለውን አገዛዝ በመፍራት ከሀገሪቱ ላለመውጣት ወስነዋል።
እናም አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ሒዩማን ራይትስ ዎች ኢትዮጵያውያኑ ከሳውዲአረቢያ ተገደው በሃይል እንዳይወጡ የሪያድን መንግስት ተማጽኗል።

እንደ ሒዩማን ራይትስ ዎች ገለጻ ከኢትዮጵያውያኑ መካከል በኢኮኖሚ ችግር ወደ ሳውዲአረቢያ የገቡ ቢኖሩም አብዛኞቹ ግን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የማይፈልጉት በፖለቲካ ችግር ጭምር ነው።
ኢትዮጵያውያኑ ወደ ሀገራቸው ቢመለሱ ባላቸው የፖለቲካ አመለካከት ሳቢያ በሀገራቸው መንግስት ሰቆቃና ግድያ ሊፈጸምባቸው ይችላል ሲል ስጋቱን ገልጿል ሒውማን ራይትስ ዎች ባወጣው መግለጫ።

በተለይ ደግሞ በኦሮሚያ ያለው ሁኔታ እጅግ አስፈሪ በመሆኑ ስደተኞቹ በፍጹም ተገደው ወደ ኢትዮጵያ መመለስ የለባቸውም ነው ያለው።

ከአመታ በፊት ሳውዲአረቢያ በሀገሯ ይኖሩ የነበሩ 160 ሺ ኢትዮጵያውያን በሃይል ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ በማስገደዷ ስደተኞቹ ከፍተኛ ሰቆቃ ደርሶባቸዋል።
የተገደሉም አሉ ሲል ሒዩማን ራይትስ ዎች ስጋቱን ገልጿል።

ሳውዲአረቢያ በተባበሩት መንግስታት አለምአቀፍ ስምምነት መሰረት ለስደተኞችና ጥገኝነት ለሚጠይቁ ሰዎች ከለላ የሚሰጠውን ሕግ አልፈረመችም።
ይህ በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከፊታቸው የተደቀነውን ሞት የሚያመልጡበት አቅምም ሆነ እድል የላቸውም ሲል አለምአቀፉ የሰብአዊ መብት ተከራካሪው ሒዩማን ራይት ዎች ገልጿል።