ሲ.ፒ.ጄ በኢትዮጵያ በእስር ላይ ያሉትን ጋዜጠኞች ለመጎብኘት ያቀረበው ጥያቄ ሳይሳካ ቀረ

ሰኔ ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-እንደ ሲፒጄ መግለጫ፤ እስረኞቹን የመጎብኘቱ ጥረት ያልተሳካው፤ የሲፒጄ ልኡካን የታሰሩ ጋዜጠኞችን መጎብኘት እንደሚችሉ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ቃል ከገቡ በሁዋላ ነው ።

የዓለማቀፉ የጋዜጠኞች ተቋም ልዑካን -ከአፍሪካ ሚዲያ ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን ባለፈው ሳምንት በ ኢትዮጵያ ባደረጉት ጉብኝት፤ ከኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትሩ ከአቶ በረከት ስምዖን ጋር ሁለት ሰ ዓታት የፈጀ ውይይት ማድረጋቸውን መግለጫው ያመለክታል።

በውይይቱ ወቅት  የሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶባቸው በ እስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኞች  እንዲለቀቁ ልኡካኑ ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ ሁለት ስዊድናውያንን ጨምሮ አምስት ጋዜኞች የሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶባቸው በ እስር ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።

የሲፒጄ ልዑካን በማያያዝም በ 2009 ዓመተ ምህረት የወጣው የ ኢትዮጵያ የፀረ-ሽብርተኝነት ህግ ፤በጋዜጠኞች ላይ እያሳደረ ያለው ጫና እና ተፅዕኖ እጅግ እንዳሣሰባቸው ለአቶ በረከት ገልፀውላቸዋል።

በ እስር ላይ ያሉትን ጋዜጠኖች እንዲገበኙ የተገባላቸው ቃል ባለመከበሩ ማዘናቸውንም ልዑካኑ አልሸሸጉም።

የሲፒጄ ቦርድ አባል  ቻርሌን ሃንተር ጐልት፦ ‹‹የታሰሩ ጋዜጠኞችን ባለመጐብኘታትንና የእነሱን ሐሳብ ባለመስማታችን አዝነናል”ብለዋል።

“ጤናማ የዲሞክራሲ ሥርዓት ፤ጠንካራና  ተቺ ሚዲያ  ያስፈልገዋል፡፡ ተቺ ሚዲያዎች በዓለማችን  በብዛት ይገኛሉ፡፡ የኢትዮጵያ ዕድገትና በዓለም ያላት ገጽታ፤  አገሪቷ ለዲሞክራሲያዊ  ማኅበረሰብ መፈጠር ከምትሰጠው ዋጋ ጋር ይያያዛል›› ሲሉም አክለዋል- ቻርለን ሀንተር።
በዚሁ ውይይት ላይ አቶ በረከት ስምዖን፦ ‹‹እስካሁን ድረስ  አንድንም ጋዜጠኛ በአሸባሪነት አልከሰስንም፤›› ማለታቸውን ሲፒጄ ጠቁሟል።

የፀረ-ሽብር ሕጉ ቅድመ ምርመራን ተግባራዊ ለማድረግ ወይም የፕሬስ ነፃነትን ለማጥቃት የወጣ ሳይሆን የሁሉንም ዜጐች ደኅንነት ለማስከበር ሲባል እንደወጣም ተናግረዋል፡፡

አቶ በረከት አያይዘውም፦‹‹ይሁንና ሕጉን በመተግበሩ አግባብ ማንኛውም ዓይነት ስህተት ካለ፤ መንግሥት ቁጭ ብሎ ራሱን ለመገምገም ዝግጁ ነው›› ማለታቸውን ሲፒጄ አውስቷል።

ኢትዮጵያውያኖቹ ጋዜጠኞች እስክንድር ነጋ፣ውብሸት ታዬ እና ርዕዮት ዓለሙ በፃፉዋቸው ነገሮች በሽብርተኝነት መከሰሳቸው፤ ማርቲን ሽብዬ እና ጆሀን ፔርሰን የተባሉት የስዊድን ጋዜጠኞች ደግሞ  ለጋዜጠኞች ክልክል ወደ ሆነውና የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወደሚፈፀምበት የኦጋዴ አካባቢ የምርመራ ሪፖርት ለመስራት ያለወረቀት ሲገቡ ተይዘው፤  ሉዓላዊነትን በመጣስ ክስ በእስር ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።
የሲፒጄው የቦርድ አባል ሃንተር ጐልት ስለ አጠቃላይ ጉብኝታቸው በሰጡት አስተያዬት፦‹‹ወደ አዲስ አበባ በመጣንበት ወቅት በመንግሥትና በግሉ ሚዲያ መካከል ከፍተኛ ልዩነት መኖሩን ሰምተን የነበረ ሲሆን፣ ይህንንም በጉብኝታችን አረጋግጠናል››  ነው ያሉት።

ጋዜጠኞችን በማዋከብ፣ በማስፈራራት፣በፈጠራ ክስ በማሰር፣ለስደት በመዳረግ እና የጋዜጠኝነት ሙያን በተለያዩ አሳሪ ህጎች በመተብተብ የምትታወቀው ኢትዮጵያ ፤  በዓለማችን ግንባር ቀደም የፕሬስ ጠላቶች ከሚባሉት አገሮች ዋነኛዋ መሆኗን የዓለማቀፍ የጋዜጠኞች እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide