ሰኔ 1 ዛሬ በተለያዩ አካባቢዎች እየታሰበ ነው

ሰኔ ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በምርጫ 97 የመለስ መንግስት የህዝብ ድምጽ ማጭበርበሩን ተከትሎ በተነሳው ተቃውሞ በግፍ የተገደሉ ኢትዮጵያውያንን በአዲስ አበባ እና በመላው አለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እየዘከሩት ነው።

ከመኢአድ የተለዩት እና በዶ/ር ታዲዮስ የሚመራው መኢአድ አባላት በዛሬው እለት በመቶዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸውን በመያዝ እለቱን አስበው ውለዋል።

22 አካባቢ ከሚገኘው የአቶ ተስፋ ድረቤ ቤት በርካታ ወጣቶች በተገኙበት ቀኑን በግጥም እና በተለያ  ስነፅሁፎች አስበው ውለዋል። የሰማእታቱ ትግል አይዳፈንም፣ ታጋይ ያልፋል ትግል አያልፍም ፣ ኢህአዴግ ግንቦት 20ን ያከብራል፣ ይሁን እንጅ አሁንም ተመሳሳይ ግፍ  እየፈጸመ ይገኛል፣ ትግሉን በእያመቱ መዘከር ብቻ ሳይሆን ሁላችንም ትግሉን እንደሻማ እየነደድን መቀጠል አለብን የሚል ይዘት ያላቸው ንግግሮችና ጽሁፎች ቀርበዋል ።

በኢንጂነር ሀይሉ የሚመራው መኢአድ  በበኩሉ  ሰማዕታቱን የፊታችን እሁድ ሰኔ 3 ቀን 2004 ዓ.ም  በጽ/ቤቱ  ይዘክራል፡፡

ተቃውሞአቸውን በሰላማዊ መንገድ በማቅረባቸው ብቻ ሰኔ 1 ቀን 1997 ዓ.ም ግድያ የተፈጸመባቸውና ለአካልና ሥነልቦናዊ ጉዳት የተዳረጉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን 7ኛ ዓመት ፓርቲው ለማሰብ ያቀደው የተለያዩ ሥነጹሑፋዊ ዝግጅቶችን በጽ/ቤቱ በማቅረብ ነው፡፡

ባለፉት ዓመታት የተጎጂ ቤተሰቦችና ወዳጆች በተገኙበት ዕለቱን ከማሰብ ባለፈ ለተጎጂዎች መጠነኛ የገንዘብ ድጋፍ ሲሰጥ መቆየቱንም ከፓርቲው ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡በተመሳሳይ ሁኔታ በጥቅምት ወር 1998 ዓ.ምምርጫ 97 ትን ተከትሎ በነበረው ሕዝባዊ ተቃውሞ በመንግስት ታጣቂዎች ሙትና ቁስለኛ የሆኑ ተጎጂ የሕብረተሰብ ክፍሎች ለማግኘት ባለመቻሉ ቀኑን ማሰብ የተቻለው የሰኔ አንዱን ብቻ ነው፡፡

የሰኔ አንድ ተጎጂዎች የተገኙትም በወቅቱ የነበሩ ነጻፕሬሶች አማካይነት ጥሪ በመተላለፉ መሆኑን ፣የጥቅምቱ ችግር ሲከሰት ግን ጋዜጦቹ እንዲዘጉና አዘጋጆቹ እሥር ቤት እንዲገቡ በመደረጉ ተጎጂዎችን ጠርቶ ለማሰሰብና ቀኑን ለመዘከር አለመቻሉን ፓርቲው አስታውሷል፡የኢሳት ቤተሰብ አባላት ቀኑን በተለያዩ ዝግጅቶች ያሰቡት ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያን በፌስ ቡክና በሌሎች የመገናኛ መንገዶች ቀኑን በተመለከተ መረጃዎችን እየተለዋወጡ ነው ምርጫ 97ን ተከትሎ የሕዝብ ድምጽ መጭበርበሩን የተቃወሙ ወገኖች ሰኔ 1 ቀን 1997 እንዲሁም ከጥቅምት 22 እስከ ህዳር 1 ቀን 1998፣ከህዳር 5 – 7 ቀን 1998 ዓ.ም አደባባይ ለተቃውሞ በመውጣታቸው በመንግስት ታጣቂዎች ለሞት፣ለመቁሰል አደጋ የተጋለጡ ሲሆን በሺ የሚቆጠሩ ወጣቶች ከየአካባቢው ታፍሰው በየእስር ቤቱ መታጎራቸው አይዘነጋም፡፡

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide