መከላከያን ጥለው የሚጠፉ ወታደሮችን የማሳደድ ዘመቻ ተጀመረ

የካቲት ፲፮ ( አሥራ ስድስት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ዘረኝነትን በመጥላት እንዲሁም በህዝብ ላይ የሚወሰደውን የግፍ እርምጃ በመቃወም ካለፉት 6 ወራት ጀምሮ የመከላከያ ሰራዊቱን እየጣሉ የሚጠፉ ወታደሮች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረ ሲሆን፣ በሚጠፉት ወታደሮች ቦታ አዳዲስ ምልምል ወታደሮችን ለመቅጠር የሚደረገው ጥረት አልተሳካም። ይህን ተከትሎም የሚጠፉ ወታደሮችን በማሳደድ በግድ እንዲቆዩ የማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። በአንዳንድ አካባቢዎች ወታደሮች ላለመያዝ በሚያደርጉት ራስን የመከላከል እርምጃ ጉዳት እየደረሰ ነው።
ባለፈው ማክሰኞ በሰሜን ሸዋ ዞን በሬማ ከተማ ከሰራዊቱ ጠፍቶ ወደ ቤተሰቦቹ የተመለሰውን ወታደር ቅጣው አወቀን የደህንነት አባላት ይዘው ያሰሩ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ሁኔታ ጠፍተው የመጡና የታሰሩ የሰራዊቱ አባላት ከወታደር አወቀ ጋር በመሆን፣ ጠዋት ላይ በጠባቂ ፖሊሶች ላይ ጥቃት ፈጽመው ሲያመልጡ የእሩምታ ተኩስ ተከፍቶባቸው ቆስለው ተይዘዋል። በተኩሱ መሃል በርካታ የቤት እንስሳት የተጎዱ ሲሆን፣ የቆሰሉት ወታደሮች በደህንነት ሃይሎች ታፍነው ተወስደዋል።
ተመሳሳይ ድርጊት በአካባቢው ባሉ ወረዳዎች ላይ መፈጸሙንም ለማወቅ ተችሎአል። የ7 አመታት ግዳጃቸውን የጨረሱ ወታደሮች መከላከያን በፈቃዳቸው ለመልቀቅ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ባገኙት አጋጣሚ መጥፋትን እንደአማራጭ ወስደውታል። በአሁኑ ሰአት 7 አመታት አገልግለው የመልቀቂያ ፈቃድ የጠየቁና መልስ የሚጠባበቁ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ የመከላከያ አባላት መኖራቸውን የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማንኛውም የመከላከያ አባል አዋጁ እስከሚጠናቀቅበት ጊዜ ድረስ የመልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባት እንደማይችል ይደነግጋል።