መንግስት በአህባሽ የእስልምና አስተምህሮ ያሰለጠናቸውን 300 ሰዎች አስመረቀ

ህዳር 28 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-በታጠቅ ወታደራዊ ማሰልጠኛ በአህባሽ የእስልምና አስተምህሮ ላይ ስልጣና የወሰዱት ሙስሊም ኢትዮጵያውያን፣ በኢትዮጵያ የሚታየውን የእስልምና አክራሪነት እንዲዋጉ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።

ስልጠናው በፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር በዶ/ር ሺፈራው ተክለማርያም፣  በአዲስ አበባ የጸጥታ ዘርፍ ሀላፊ በኮማንደር መኮንን አሻግሬ እና የአህባሽን አስተምህሮ በሚከተሉ ሙስሊሞች አማካኝነት መሰጠቱ ታውቋል።

ለሰልጣኞቹ የተሰጠው ስልጠና በዋነኝነት ያተኮረው ፣ አህባሽ የተባለው የእስልምና እምነት አገርበቀል በመሆኑ ማንኛውም በአገሪቱ ውስጥ የሚገኝ ሙስሊም እንዲከተለውና መጤ የሆነውን የዋህቢዝም አክራሪነት አስተሳሰብ እንዲታገለው የሚያያደርግ ነው።

በርካታ በውጭ አገር የሚኖሩ ሙስሊሞች መንግስት በሀይማኖት ጉዳዮች ጣልቃ በመግባት፣ የእስልምና እምነት ተከታዮችን ለመከፋፈል የሚያደረገውን ሙከራ ማውገዛቸው ይታወሳል።

መንግስት እየተከተለው ያለው ፖሊሲ፣ በሙስሊሞች መካከል ከፍተኛ ልዩነት እንዲፈጠር ማድረጉን መረጃዎች የሳያሉ።

በአዲስ አበባ የሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች ሙስሊሙ ማህበረሰብ ለእምነቱ ዘብ እንዲቆም የሚያሳስብ ወረቀት መበተናቸው ይታወሳል።

በአሁኑ ጊዜ አንዋር መስጊድ አካባቢ ጥብቅ የደህንነት ጥበቃ እየተካሄደ መሆኑን የአዲስ አበባ ዘጋቢያችን አመልክቷል።