መምህር የሰው ወንድሙ ከአራት ወራት እስር በኋዋላ በነጻ ተለቀቀ

ግንቦት ፲፮ ( አሥራ ስድስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት ቤት የሕክምና መምህር ፣ የተቋሙ ዲን እንዲሁም ተመራማሪ የሆነው ወጣት የሰው ወንድሙ ማሙዬ ለአራት ወራት በማእከላዊ እስር ቤት ሲሰቃይ ቆይቶ በነጻ ተለቋል። የሰው ወንድሙን የታሰረው “ አንድ ተጠርጣሪ የሆነ ግለሰብን መኖሪያ ቤትህ ለአንድ ቀን አሳድርሃል፣ እንዲሁም ከግንቦት 7 ጋር ግንኙነት አለህ” የሚሉ መረተቢስ ውንጀላቸው ቀርበውበት ሲሆን፣ ሁሉም ክሶች በመጨረሻ ውድቅ ተደርገዋል።
መምህር የሰው በተለያዩ የአሜሪካ የሕክምና ማእከላት ጆርናሎች የምርምር ሥራዎቹን አሳትሟል። እስከሚታሰርበት ጊዜም ኢትዮጵያን በመወከል ወደ አሜሪካ በማቅናት በግል እና በቡድን ሥራዎች ላይ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ነበር።
በእስር ላይ እያለ ጎንደር የሚገኙት ወላጆቹ የልጃቸውን ሁኔታ ማወቅ ሳይችሉ ቆይተዋል። እንግዳ ቤተሰብ እና ጓደኛን ማሳደር እንደወንጀል መቆጠሩ የህወሃት ኢህአዴግ ሥርዓት ምን ያህል ከሕግ አግባብ ውጪ ዜጎችን እንደሚያፍን ማሳያ ነው ሲሉ ምንጮቻችን ገልጸዋል።
በማእከላዊ እስር ቤት ውስጥ ከአማራ እና ኦሮምያ አካባቢዎች የመጡ በርካታ መምህራንና ምሁራን ታስረው እንደሚገኙም ምንጮች ገልጸዋል።