ለጣና ሃይቅ ህልውና ማጣት ምክንያት የሆኑ 8 አበይት ችግሮች መኖራቸው ተገለጸ  

 

(ኢሳት ዜና –ሐምሌ 20/2009)ባለሙያው አቶ ማስተዋል እጅጉ እንደገለፁት የጣና ሐይቅ በውሃ አስተዳደር መርህ መሰረት አለመያዙ በህልውናው ላይ ትልቅ አደጋ ደቅኗል። በሀይቁ ላይም 8 ዋና ዋና የሚባሉ አብይ ችግሮች መኖራቸውንም ባለሙያው ይገልፃሉ። እነዚህም በደለል መሞላት፣ የባህር ሽሽ መሬት መጨመር፣ ውሃውን ማፍሰስ እና በተለያዩ ሰበቦች እንዲቀንስ ማድረግ፣ በተለይ በኬሚካሎች መበከል፣ እንዲሁም የባክቴሪያ መብዛት፣ እምቦጭን በመሳሰሉ አረሞች መወረር፣ ፍሳሽ ቆሻሻን መልቀቅ እና ያልተጠኑ ግንባታዎችን በጣና ዙርያ መገንባት ናቸው። ከእነዚህም የዋና ዋና ችግሮች ተለይተው ለ3ቱ ለጣና ሐይቅ መጥፋት ምክንያቶች የሆናሉ ነው ያሉት። የውሃ የውሃ አስተዳደር ባለሙያው አቶ ማስተዋል እጅጉ።

የጣና ውሃ ለሐይድሮ ኤሌክትሪክ ሐይል በሚል ወደ ጣና በለስ በከፍተኛ መጠን ሲቀየስ ሚዛኑን እንዲጠብቅ ሳይደረግ መከናወኑ ለሐይቁ አደጋ ምክንያት መሆኑን ባለሙያዎች ተናግረዋል።

ይህ ባለበት ሁኔታም በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ። በአሁኑ ጊዜ የጣና ሐይቅ በእንቦጭ አረም መወረሩና ይህንንም ለማስወገድ ጥረት አለመደረጉ ሕልውናው አደጋ ላይ እንዲወድቅ አድርጎታል ብለዋል።

እንደ ውሃ አስተዳደር ባለሙያው አቶ ማስታዋል እጅጉ ገለፃ በጣና ዙሪያ የተሰሩ ሆቴሎችና ድርጅቶች ፍሳሽ ቆሻሻቸውን መልቀቃቸውም ተገቢ አይደለም።

እናም የጣናን ሐይቅ ለማዳን ሀገራዊ ጥሪ ካልተደረገና ዘላቂ የውሃ አስተዳደር ካልተዘረጋለት በዘመቻ ብቻ ከመጥፋት ማዳን እንደማይቻል ባለሙያው አሳስበዋል።

ይህ ካልሆን ይላሉ የውሃ አስተዳደር ባለሙያው አቶ ማስተዋል እጅጉ ይህ ካልሆነ የጣና ሐይቅ እንደ ሌሎችም ሆነ እንደ ዓለማያ ሐይቅ ሕልውናው ጠፍቶ ተረት ተረት ሆኖ ሊቀር ይችላል።