ለደቡብ ሱዳን ሰላም መስፈን ከጎረቤት አገራት ውጭ ያሉ አገሮች ሙከራ ማድረግ እንዳለባቸው የአሜሪካው አምባሳደር ተናገሩ

የካቲት ፲፬ ( አሥራ አራት )ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሱዳንና ደቡብ ሱዳን የአሜሪካ ልዩ ልዑክ የሆኑት አምባሳደር ዶናል ቡዝ በለንደን ሻተም ሃውስ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር የአካባቢው አገራት የራሳችውን ጥቅም ለማስከበር ሲሉ የደቡብ ሱዳንን የሰላም ሂደት እያወሳሰቡት ነው ብለዋል።
አንዳንድ ጊዜ እነዚህ አገራት በሂደቱ ላይ በቀጥታ ተጽእኖ የሚያደርጉ ሲሆን፣ አንዳንድ ጊዜ የውይይቱን አቅጣጫ ሁሉ እስከማስቀየር ይደርሳሉ ። አንዳንዶች ሸምጋይ መሆን ሲገባቸው የግጭቱ ተሳታፊዎች ሆነዋል የሚሉት አምባሳደሩ፣ አንዳንድ የደቡብ ሱዳን ሃይሎች ከጎረቤት አገራት ድጋፍ በመፈለግ የሰላም ሂደቱን እያደናቀፉት ነው ሲሉ አክለዋል።
ምንም እንኳ ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ የሚል አቋም በአህጉሪቱ ቢኖርም፣ አስፈላጊነቱና ጥቅሙ እንደአካባቢው ሁኔታ እንደሚለያይና በእርሳቸው እምነት ለደቡብ ሱዳን የሰላም መፍትሄ ማምጣት ያለባቸው በቀጥታ ጥቅም ያላቸው የጎረቤት አገራት ከሚሆኑት ይልቅ ራቅ ያሉ አገሮች ቢሳተፉት ይሻላል ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል።

አምባሳደሩ ምንም እንኳ የጎረቤት አገራቱን ስም ባይጠቅሱም፣ በደቡብ ሱዳን በሽምግልና ስም ስራዎችን የሚሰሩት አገራት ኢትዮጵያ፣ ዩጋንዳና ኬንያ መሆናቸው ይታወቃል። በተለይ የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ የሽምግልና ጥረቱን በዋናነት ይዞ ለአመታት ሲሰራበት ቢቆይም የተባለውን ሰላም ማስፈን አልቻለም። የአምባሳደር ቡዝ ንግግርም በዋናነት ኢትዮጵያ ላይ ትኩረት ያደረገ ሊሆን እንደሚችል ዘጋቢያችን አስተያየቱን አስፍሯል።