ለዓባይ ግድብ መዋጮ ያለ ያለ ፍላጎቴ ከደመወዜ ተቆርጦብኛል ያሉ አንድ መምህር ክስ መመስረታቸውን አዲስ አድማስ ዘገበ

ታህሳስ 28 ቀን 2004 ዓ/ ም

ኢሳት ዜና:-ለዓባይ ግድብ መዋጮ ያለ ያለ ፍላጎቴ ከደመወዜ ተቆርጦብኛል ያሉ አንድ መምህር ክስ መመስረታቸውን አዲስ አድማስ ዘገበ።

በድል በትግል ትምህርት ቤት ለረዥም ዓመታት በመምህርነት ያገለገሉት አቶ ግርማ በፈቃዱ “ያለ ፈቃዴ ለ ዓባይ ግድብ በማለት ከደመወዜ ቆርጦብኛል  በማለት ክስ የመሰረቱት በሚያስተምሩበት  ትምህርት ቤት ላይ ነው።

ትምህርት ቤቱ በ አባይ ግድብ መዋጮ ዙሪያ ከትምህርት ቤቱ መምህራን ጋር ሲወያይ ሰብሳቢዎቹ  እያንዳንዱ መምህር ከደመወዙ 20 በመቶ እንዲያዋጣ ቃል ባስገቡበት ጊዜ – መምህር ግርማ ተቃውሞ አሰምተው እንደነበር የጠቀሱት  የጋዜጣው ምንጮች፤ትምህርት ቤቱ ግን ተቃውሟቸውን ሳይቀበለው ከደመወዛቸው እንዲቆረጥ በማድረጉ ክስ መመስረታቸውን ተናግረዋል።

መምህሩ -በትምህርት ቤቱ ላይ ክስ የመሰረቱት በጉለሌ ክፍለ-ከተማ ፍርድ ቤት ሲሆን፤ በአሁኑ ጊዜ የችሎት ክርክሩ እየቀጠለ እንደሚገኝ ምንጮቹ ገልጸዋል።

ትምህርት ቤቱ በበኩሉ፤  ስለ ዓባይ ግድብ መዋጮ መምህራንን ባወያየበት ወቅት  ከመምህራን ደመወዝ ላይ 20 በመቶ እንዲቆረጥ የተደረሰበትን ውሳኔ መምህር ግርማ እንደተቃወሙት ባይክድም፤ከሁሉም የትምህርት ቤቱ ሠራተኞች ደመወዝ ላይ ሲቆረጥ ከእርሳቸውም ደመወዝ ላይ  ይቆረጥ በማለት እንደቆረጠ ገልጿል።

መንግስት የኣባይ ግድብን መዋጮ አስመልክቶ የግለሰቦች የፈቃደኝነት ፊርማ እስከሌለ ድረስ አስገድዶ ማስከፈል አይቻልም የሚል የይምሰል መግለጫ ቢያወጣም፤ በተግባር ግን መዋጮውን ላለመክፈል ያንገራገሩ ሁሉ ፦”ፀረ-ህዝብና ፀረ-ልማት” እየተባሉ ለተለያዩ አስተዳደራዊ በደሎች በመጋለጣቸው፤ብዙዎች የሚደርስባቸውን ቅጣት በመፍራት ያለ ፍላጎታቸው ለመክፈል መገደዳቸው ይታወቃል።

ኢሳት በድል ትግል ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ መምህራን ለአባይ ግድብ መዋጮ አናወጣም በማለት ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ሲወዛገቡ እንደነበር ከወራት በፊት መዘገባችን ይታወሳል።