ለስደተኞች የተሰጠው የጊዜ ገደብ እንዲራዘም በኢትዮጵያ የቀረበው ጥያቄ በሳኡዲ በኩል ምላሽ አልተሰጠውም።

ሰኔ ፲፭( አሥራ አምስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሳኡዲ ያሉ ስደተኞች ሀገሪቱን ለቀው የሚወጡበት ቀነ ገደብ እንዲራዘም ጥያቄ ማቅረቡን የኢትዮጵያ መንግስት ገለጸ።
ይሁንና ቀነ ገደቡ ሊጠናቀቅ የቀረው ጊዜ በጣም አጭር በመሆኑና በዚህ አጭር ጊዜ ሁሉንም ስደተኞች መመለስ እንደማይቻል በመረዳት ጊዜው እንዲራዘም ጥያቄ ማቅረቡን ቢገልጽም እስካሁን ከሳኡዲ በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም።
በሳኡዲ በኩል ለሦስት ወራት የተሰጠው የስደተኞች መውጫ የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ናቸው የቀሩት።አንዳንድ ቀደም ካሉት ጊዜያት ጀምሮ የተጠናከረ እንቅስቃሴ ያደረጉ ሀገራት ዜጎቻቸውን ሙሉ በሙሉ የመለሱ ሲሆን፤ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በጉዳዩ ዙሪያ ይህ ነው የሚባል ሥራ ያልሠራው የኢህአዴግ መንግስት ግን ባለቀ ሰዓት ስደተኞች ወደሀገራቸው እንዲገቡ ቅስቀሳ ማድረግ ጀምሯል።
የጊዜ ገደቡ ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት በቀሩበት በአሁኑ ወቅት በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እዚያው ሳኡዲ ይገኛሉ። ተጨማሪ ቀናት እንዲፈቀድለት የጠየቀው የኢህአዴግ መንግስት በሳኡዲ በኩል ምላሽ ባለማግኘቱ “እኛ ቀነ ገደብ ይራዘማል ብለን ለስደተኞች ተስፋ አንሰጥም። ባሉት ጥቂት ቀናትም ቢሆን ለቀው መውጣት አለባቸው” ብሏል።
በሪያድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የዲያፖራ ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት አቶ ፈይሰል መንግስታቸው የጊዜ ገደቡ እንዲራዘም ለሳኡዲ መንግስት ጥያቄ ማቅረቡን በመጥቀስ “ነገር ግን የተጠየቀው ቀን ይጨመራል ወይስአይጨመርም በሚለው ጉዳይ እርግጠኛ መሆን አንችልም” በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል።