ለስኳር ፕሮጄክቶች ግንባታና ማስፋፊያ ከህንድ የተወሰደው ከ700 ሚሊዮን ዶላር በላይ ብድር የታሰበውን ውጤት አለማምጣቱ ተገለጸ

ኢሳት (መጋቢት 11 ፥ 2009)

የኢትዮጵያ መንግስት በተለያዩ ጊዜያት ከህንድ ለስኳር ፕሮጄክቶች ግንባታና ማስፋፊያ የወሰደው ከ700 ሚሊዮን ዶላር በላይ ብድር (ከ140 ቢሊዮን ብር በላይ) የታሰበውን ውጤት አለማምጣቱ ተገለጸ።

ለእነዚሁ ፕሮጄክቶች በአምስት ዙሮች በድምሩ 739 ሚሊዮን ዶላር ብድር መለቀቁንና ባንካቸው ፋይናንስ ያደረጋቸው የስኳር ልማት ፕሮጄክቶች ውጤታማ መሆን እንዳልቻሉ የህንድ የኤክስፖርትና ኢምፖርት (ኤግዚም) ባንክ ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆኑት ዲባሲህ ማሊክ ለሪፖርተር ጋዜጣ አስታውቀዋል።

የህንድ ባንክ ነባሮቹን የወንጂና መተሃራ ስኳር ፋብሪካዎች የማስፋፊያ ፕሮጄክቶችን ፋይናንስ ከማድረግ ባሻገር ለተንዳሆ የተቀናጀ ስኳር ልማት ፕሮጄክትም ብድር ማቅረቡን ሃላፊው አውስተዋል።

ይሁንና በተንዳሆና በሌሎች የስኳር ፕሮጄክቶች ላይ መጓተቶች ከመታየታቸው በተጨማሪ በብድር ሲካሄዱ የነበሩት የልማት ስራዎች ውጤት እንዳላመጡ የህንዱ ኤግዚም ባንክ ሃላፊ ዲባሲህ ማሊክ አክለው ገልጸዋል። ከህንድ በተገኘ ብድር ስራቸው ተጀምሮ የነበሩና የማስፋፊያ ግንባታ የተካሄደላቸው የስኳር ፋብሪካዎች እንደፈረጆቹ አቆጣጠር በ2015 አም ኢትዮጵያን ስካር ላኪ ሃገር ያደርጓታል ተብሎ ሲጠበቅ እንደነበር ይታወሳል።

ይሁንና ፕሮጄክቶቹ በታቀደላቸው ጊዜ ባለመጠናቀቃቸው ምክንያት መንግስት ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰበት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ምንጮች ለኢሳት ሲገልጹ ቆይተዋል።

ያለግልፅ ጨረታ ለፋብሪካ ግንባታዎቹ ሲሰጡ የነበሩ ስራዎች እንዲሁም የእቃ ግዢዎች በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ገንዘብ እንዲባክን ማድረጉንና የስኳር ኮርፖሬሽን አመራሮች ለፕሮጄክቶቹ መጓተት ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው ምንጮች አስረደተዋል።

አቶ አባይ ጸሃዬ የኮርፖሬሽኑ ሃላፊ ሆነው ባገለገሉበት ጊዜ የስኳር ፕሮጄክቶቹ የስራ እንቅስቃሴ ቢጀመርም በመሃል ምክንያቱ ባልተገለፀ መንገድ ከአምስት የሚበልጡ የአዳዲስ የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ ተቋርጦ መቆየቱን የልማት ባንክ ምንጮች በተለያዩ ጊዜያት ሲገልፁ ቆይተዋል።

የህንዱ ኤግዚም ባንክ በተለያዩ ጊዜያት ለእነዚሁ የስኳር ፕሮጄክቶች የ122, የ166, የ213, የ91 እንዲሁም የ47 ሚሊዮን ዶላር ብድሮችን በአምስት የብድር ማዕቀፎች መለቀቃቸውን የአበዳሪው ባንክ ሃላፊዎች ለጋዜጣው አስረድተዋል።

የስኳር ፕሮጄክቶቹ ወደ ምርት ሳይገቡ ብድር የመክፈያ ጊዜያቸው መቃረቡን የስኳር ኮርፖሬሽን ከወራት በፊት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ከሁለት አመት በፊት ስኳርን ለውጭ ገበያ ተቃርባለች ተብላ የነበረው ሃገሪቱ በአሁኑ ወቅት የስኳር እጥረት አጋጥሟት በመገኘቱ ምክንያት ስኳር ከውጭ ሃገር እንዲገባ በመደረግ ላይ እንደሚገኝ ለመረዳት ተችሏል።

የስኳር ፋብሪካዎቹ ወደ ስራ ባለመግባታቸው ምክንያት ለፋብሪካዎቹ ግብዓት ሊቀርቡ የነበሩ እና በሚሊዮን ብር የሚቆጠር ገንዘብ የፈሰሰበት የሸንኮራ አገዳ ምርት እንዲወገድ መደረጉም ሲዘገብ ቆይቷል።

መንግስት በጋምቤላ ክልል ለሰፋፊ እርሻ ልማት ፕሮጄክቶች ሲሰጥ በነበረው ብድር ላይ የደረሰበት ከፍተኛ ኪሳራ ተመሳሳይነት ያለው እንደሆነም የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።