ህዝባዊ ተቃውሞው የበጀት እጥረት ፈጥሮብናል ዋጋም አስከፍሎናል ሲሉ አመራሮች ተናገሩ

መጋቢት ፲፱ (አሥራ ዘጠኝ)ቀን ፪፲፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኦሮምያና በአማራ ክልሎች ተነስቶ በነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ የተነሳ ወረዳዎች ስራ መስራት አቁመው ትኩረታቸውን ሁሉ ተቃውሞውን ወደ መከላከል አድርገው እንደነበረና ይህንን ተቃውሞ ለመቆጣጠር ለወረዳዎች የተበጀተውን በጀት በማጥፋታቸው ከፍተኛ የበጀት እጥረት መከሰቱን የተለያዩ አመራሮች ተናግረዋል።
የፐብሊክ ሚኒስቴር ሃላፊዎች ከክልል አመራሮች ጋር በተወያዩበት ወቅት እንደተገለጸው፣ የክልሎች ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮዎች እስከ ወረዳ የሚደርሱ 31 የተለያዩ የመንግስት ተቋማት፣ ህዝባዊ አመጹን ለመቆጣጠር በወጣው ከፍተኛ ወጪ የተነሳ የበጀት እጥረት ያጋጠማቸው በመሆኑ ስራ እያቆሙ ነው።
የተለያዩ ተቋማት ያቀዱትን እቅድ ለማሳካት የሚያስችል በጀት በማጣታቸው ተዘዋውረው ለመስራትም ሆነ ወደ ገጠር ተጉዞ ክትትል ለማድረግ ባለመቻሉ በኦሮምያና አማራ ክልሎች ስራዎችን መስራት በማይቻልበት ደረጃ ተደርሷል።
ግሎባል ፈንድ በኢትዮጵያ የኤች አይ ቪ ቫይረስ ስርጭትን ለመቆጣጠር ቀደም ብሎ ሲያደርገው እንደነበረው ሁሉ በዚህ አመትም ገንዘብ እንደሚለግስ ቃል ገብቶ የነበረ ቢሆንም፣ ገንዘብ ለመልቀቅ ፈቃደኛ ሆኖ ባለመገኘቱ ከፍተኛ የበጀት እጥረት እንዳጋጠመ፣ የመንግስት በጀት አስተዳደር ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት አቶ ካህሳይ ሳእለ እግዚአብሄር ተናግረዋል። አቶ ካህሳይ አክለውም በጀት ከለጋሾች በተለይም ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (UNDP) እና ግሎባል ፈንድ ከመሳሰሉ ለጋሾች ከሚገኝ እርዳታ የሚመነጭ ቢሆንም ፣ ለ2009 ዓም የሲቪል ሰርቪስ ስራዎች ለጋሾች ከተፈጠረው ተቃውሞ ጋር ተያይዞ እርዳታ ባለመስጠታቸው መንግስት የበጀት እጥረት አጋጥሞታል ብለዋል።
ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም፣ የአውሮፓ ህብረትና ሌሎችም ለጋሽ አገራት የሰጣል ተብሎ ቃል የተገባው ገንዘብ እንዲለቀቅ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብም እስካሁን ድረስ ምንም አይነት ድጋፍ እንዳልተገኘ የገለጹት አቶ ካህሳይ ፣ በዚህም የተነሳ መንግስት ከካዝናው ያለውን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ በመጠቀሙ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የበጀት ክፍተታቸውን የሚሞሉበት ገንዘብ የላቸውም ብለዋል።
ግሎባል ፈንድ፣ የአውሮፓ ህብረት እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ምላሻቸው ቀናኢነት የጎደለው ነው የተባለ ሲሆን፣ በአገሪቱ የሚገኙ 68 ኩባንያዎች የውጭ ምንዛሬ የለም በማለት ስራቸውን ለማቆም እየተገደዱ ነው። የምድር ባቡት ኮርፖሬሽን ስራተኞችን በትኖ ስራ ለማቆም መገደዱም ታውቋል። በአዲስ አበባ የታሰበው የማስፋፊያ ፕሮጀክት በበጀት እጥረት ምክንያት መቆሙንም ምንጮች ገልጸዋል።
የመከላከያው ብረታብረት ኮርፖሬሽን (ሜቴክ)፣ መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ፣ አምቼ፣ ማሩ፣ በላይ አብ ሞተርስና ሊፋን የተባሉ ኩባንያዎችን ጨምሮ 68 የአገሪቱ ማኑፋክቸሪንግ ኩባንያዎች፣ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ስር በሚገኘው ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲቲዩትና በሜቴክ በኩል ለፓርላማው ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡት አቤቱታ፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት በአፋጣኝ ካልተፈታ ስራቸውን ለመቀጠል የማይችሉበት ደረጃ ደርሰዋል።
ንግድ ባንክ ለ40/60፣ ለ20/80 እና 10/90 የቤቶች ልማት የሚሰበስበው ገንዘብ ችግሩን እንዳላቃለለውም በውውይቱ ወቅት ተነስቷል።
አመጹ የመቀጠል አዝማሚያ ካሳየ ፣ በመንግስት በጀት ላይ የሚደርሰው መቃወስ ከዚህም በላይ ይሆናል ሲሉ አቶ ካህሳይ አስጠንቅቀዋል።