ህወኃት የነጻነት ታጋዮችን ለማደን ብዛት ያለው ወታደር አሰማራ። የአርበኞች ግንቦት 7 የሰሜን ኢትዮጲያ ዕዝ ሊረሸኑ የነበሩ ወንድማማቾችን ታደገ

ሰኔ ፲፭( አሥራ አምስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ህዝባዊ ወያነ ኃርነት ትግራይ -ህወኃት በመተማና በጭልጋ አካባቢ ያሉ የነጻነት ታጋዮች ላይ ጥቃት ለመፈጸም በርካታ ወታደሮችን ወደስፍራዎቹ ማንቀሳቀሱ ተገለጸ።
ታጋዮቹ ያሉበትን ሥፍራ ማወቅ የተሳናቸው የህወኃት ታጣቂዎች በትናንትናው ዕለት ወደታጋዮቹ ዘመዶች ቤት በመሄድ አሠሳ ከማድረጋቸውም በላይ ታጋዮቹ ያሉበትን ቦታ ተናገሩ በማለት ዘመዶቻቸውን ሲያስጨንቁ አምሽተዋል።
ዘመዶቻቸው የታጋዮቹን አድራሻ እንደማያውቁ ቢገልጹም “ያሉበት ካልጠቆማችሁ እናንተ ላይ እርምጃ ይወሰድባችኋል” የሚል ዛቻና ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።
የሻሃር ቀበሌ ነዋሪዎች በተለይ ለኢሳት እንደገለጹት የህወኃት ልዩ ወታደሮች በዛሬው ዕለት የታጋዮቹን ዘመዶች ከፊት እንደ መሪ በማሰለፍ የነጻነት አርበኞቹን ለማሰስ በስፋት ተሰማርተዋል።
ዛሬ ልክ ከጧቱ 2፡00 ሰዓት ላይ ወደ አካባቢው ተጨማሪ ልዩ ወታደሮች መድረሳቸውን የገለጹት ነዋሪዎቹ፤ ዛሬ የገቡት ወታደሮች ትናንት ከደረሱት ጋር በመሆን በጭልጋና መተማ ወረዳዎች አሠሳ ሲያደርጉ ውለዋል።
ይሁንና ህወኃት ዘመዶቻቸውን ጭምር በማስገደድ በአካባቢው እጅግ በርካታ ልዩ ወታደሮችን ቢያሰማራም፤እስካሁን ድረስ የነጻነት ታጋዮቹ ሊገኙ አለቻላቸው ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የወያኔ ስርዓት ሌሊት ላይ ከእስር አውጥቶ ሊረሽናቸው የነበሩ ሁለት ወንድሟሟቾችን የአርበኞች ግንቦት 7 የሰሜን ኢትዮጲያ ዕዝ እንደታደጋቸው ለዝግጅት ክፍላችን የደረሰው መረጃ ያመለክታል።
ሰኔ 14 ቀን 2009ዓ/ ም ከሌሊቱ 6:ሰዓት ከ 20 ደቂቃ ሲሆን በሰሜን ጎንደር ዞን ጭልጋ ወረዳ የህወኃት ታጣቂዎች አስማረ ሲሳይ በቀለ እና ገላጋይ ሲሳይ በቀለ የተባሉ የአለፋ ወረዳየሻውራ ከተማ ተወላጅ የሆኑ ወንድማማቾችን ሌሊት ከእስር ቤት በማውጣት ሊረሽኗቸው ሲሉ ነው የግንባሩ ዕዝ የታደጋቸው።
ታጣቂዎቹ ወጣቶቹን በዱላ እየደበደቡ ወደ ኳሂር ቀበሌ ለመረሸን ሲወስዷቸው የአካባቢው ህብረተሰብ በቦታው ለሚንቀሳቀሱ የአርበኞች ግንቦት 7 ታጋዬች ጥቆማ ማድረጋቸውን የሚያመለክተው ይኸው መረጃ፤ ታጋዬችም በፍጥነት በቦታው በመድረስና ከህወኃት ወታደሮች እና ፀረ ሽብር አባላት ጋር በመታኮስ ወጣቶቹን እንደታደጓቸው ይገልጻል።
ወንድማማቾቹ አስማረ ሲሳይ በቀለ እና ገላጋይ ሲሳይ በቀለ በአሁኑ ሳዓት በጥሩ የጤንነት ሁኔታ ከታጋዬችጋር እንደሚገኙና ቃለ መጠይቅ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን የጠቀሰው ወታደራዊ መረጃው፤ ታጋዬቹም ተል ዕኳቸውን በመፈጸም በሰላም ወደ ቦታቸው መመለሳቸውን ጠቅሷል።